በማህበራዊ ሚዲያ የሃሰት ዜናዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችን የሚገራ ህግ እየተዘጋጀ ነው ተባለ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመንግስት ዓመታዊ ዕቅድ ዙሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተከፍሏቸው የሃሰት ዜናዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች መኖራቸውን መንግስት ደርሶበታል።
እነዚህ ግለሰቦች ህዝቡን በማደናገር ከተለያዩ አካላት ጥቅም የሚያገኙ እና የሚከፈላቸው ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ያልታወቁ ግለሰቦችን ሃሳብ ከመቀበል እንዲታቀቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አክለዉም እንዲህ ያሉ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ ህግ እያዘጋጀን ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የመገናኛ ብዙሃን እና ባለሞያዎች ለውጡ እንዲቀጥል ለማድረግ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የሚዲያ ነፃነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
በቂ የገቢ ምንጭ የሌላቸው ሚዲያ ተቋማት ከመርህ እንዳይወጡ እና ወገንተኛ እንዳይሆኑ ስፖንሰሮችና የሚመለከታቸው ተቋማት እገዛ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።