የስሎቬንያ ፕሬዝዳንት ቦሩት ፓሆር የሶስት ቀናት ኦፊሴላዊ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ተመልሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከአገራችን አቻቸው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለና ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት ጋር ውይይቶችን አካሂደዋል።
በጉብኝቱ ኢትዮጵያና ስሎቬንያ በኢንቨስትመንትና ንግድ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ፣ ፍልሰትንና ሽብርተኝነትን ጨምሮ በአህጉራዊ ሰላምና አለምዓቀፍ የጋራ አጀንዳዎች ላይ የሁለትዮሽና በአውሮፓ ህብረት በኩል የባለብዙ ወገን ትብብራቸውን ለማስፋት መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በንብ ማነብ የቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድም ለሌሎች ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ትብብር ለማድረግ መስማማት ላይ የተደረሰ ሲሆን ፤ ከመንግስት ለመንግስት ትብብሩ በዘለለ የስሎቬንያ ባለሃብቶች በዘመናዊ የማር ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማስተዋወቅና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በመጪው ሜይ ወር በስሎቬንያ በሚካሄዱ አለምዓቀፍ የንብ ቀን እና የአፍሪካ ቀን ስብሰባዎች ላይ የኢትጵያ ልኡክ እንዲሳተፍ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በሁለቱ አገሮች ፓርላማዎች መካከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግም መግባባት ላይ ይተደረሰ ሲሆን ፕሬዝዳንት ቦሩት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እና የህዝብ ወካዮች ም/ቤት አመራሮች በአገራቸው ጉብኝት እንዲያደርጉም ጋብዘዋል።