የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጎላን ተራሮች ለሶሪያ እንዲመለሱ ውሳኔ አሳለፈ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጎላን ተራሮች ለሶሪያ እንዲመለሱ ውሳኔ አሳለፈ
አርትስ 15/04/2011
እስራኤል እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1967 በሀይል የያዘቻቸውን የጎላን ከፍታዎች ለባለንብረቷ ሶሪያ እንድትመልስ በከፍተኛ የድጋፍ ድምፅ አፅድቋል፡፡
ኢራን ፐሬስ እንደዘገበው የድርጅቱ አባል ሀገራት በ151 ድጋፍ፣ በሁለት ተቃውሞ፣ እና በ14 ድምጸ ተዓቅቦ ነው ውሳኔውን ያፀደቁት፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ያፀደቀውን የውሳኔ ሀሳብ በብቸኝነት የተቃወሙት ራሷ እስራኤል እና የቅርብ አጋሯ አሜሪካ ናቸው፡፡
አሜሪካ የሶሪያ መንግስት አካባቢውን ለማስተዳደር የሚያስችል አቅም የለውም በማለት ውሳኔውን የተቃወመችበትን ምክንያት አስረድታለች፡፡
በድርጅቱ የሶሪያ ተወካዮች በበኩላቸው እስራኤል በጎላን ተራሮች የድንበር አካባቢዎች የምትፈፅመው ጥቃት ዓለም አቀፉን ህግ የሚፃረር በመሆኑ ከድርጊቷ እንድትታቀብ አሳስበዋል፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ጠቅላላ ጉባኤው ባወጣው መግለጫ እስራኤል የፀጥታው ምክር ቤት በፈረንጆቹ 1981 ያወጣውን የመፍትሄ ሀሳብ አለማክበሯን አውግዟል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤውም የድርጅቱ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቀጣዩ ስብሰባ አዲስ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊነቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡
እስራኤል የጎላን ተራሮችን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1967 በተደረገው የ6ቱ ቀን ጦርነት ነው ወደ ራሷ ግዛት በሀይል የጠቀለለችው፡፡