ሃሪ ኬን በጉዳት እስከ መጋቢት ወር ወደ ጨዋታ አይመለስም ተባለ
የቶተንሃም ሆትስፐር አጥቂ እንግሊዛዊው ሃሪ ኬን ክለቡ ማንችስተር ዩናይትድን አስተናግዶ የ1 ለ 0 ሽንፈት ባስተናገደበት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በደረሰበት የቁርጭምጭሚት ጅማት ጉዳት፤ እስከ መጭው መጋቢት ወር ድረስ ለቡድኑ ግልጋሎት እንደማይሰጥ ተነግሯል፡፡
ስፐርሶች እንዳሉት የ25 ዓመቱ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበል በመጋቢት ወር መጀመሪያ ወደ ልምምድ ሜዳ ይመለሳል ብለዋል፡፡
በያዝነው የውድድር ዓመት ለቶተንሃም 20 ጎሎችን በማበርከት ዋና ግብ አስቆጣሪ የሆነው ሀሪ ኬን ክለቡ በፕሪምየር ሊግ መርሀግብሮች እና በካራባዎ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ የሚያደርጋቸውን ግጥሚያዎች ጨምሮ በቻምፒዮንስ ሊግ ከዶርትሙንድ ጋር በሚከናወኑ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አይሰለፍም፡፡
ኬን በግራ ቁርጭምጭሚቱ ላይ የደረሰበት ጉዳት በፊል ጆንስ እና ቪክቶር ሊንደሎፍ በተሰራበት ጥፋቶች ነው ተብሏል፡፡
የተጫዋቹን ጉዳት ተከትሎ አርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ችግር ውስጥ ናቸው፤ ምክንያቱም በበጀት እጥረት ተጫዋች እያስፈረሙ ባለመሆኑ፤ የቡድኑን ዋና ግብ አስቆጣሪ ከማጣታቸው በላይ ሌላኛው መመኪያቸው ደቡብ ኮሪያዊው ሶን ሂንግ ሚን በእሲያ ዋንጫ ሀገሩን ለማገልገል በማቅናቱ ነው፤ አሁን ያላቸው ተስፋ በተጠባባቂ የአጥቂ ተጫዋቾቻቸው ፈርናንዶ ሎሬንቴ እና ቪንሰንት ያንሰን ላይ ሁኗል፡፡