ሊቨርፑል ለንደን ላይ በዌስት ሃም ዛሬ ምሽት ይፈተናል
ሊቨርፑል ለንደን ላይ በዌስት ሃም ዛሬ ምሽት ይፈተናል
የ25ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይከናወናል፡፡
የምዕራብ ለንደኑ ዌስት ሃም ዩናይትድ በለንደን የኦለምፒክ ስታዲየም ሊቨርፑልን የሚገጥም ይሆናል፡፡
አጥቂው ማርኮ አርናቶቪች፣ ግብ ጠባቂው ሉካስ ፋቢያንስኪ እና አሮን ክሬስዌል ከጉዳት ተመልሰው፤ ለመዶሻዎቹ ግልጋሎት ሊሰጡ እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ሳሚር ናስሪ ግን በባት ጉዳት ምክንያት ከምሽቱ ግጥሚያ ውጭ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በቀያዮቹ በኩል ደግሞ በቅጣት የሌስተሩ ጨዋታ ያመለጠው ጀምስ ሚልነር ለዚህ ጨዋታ መሰለፍ ይችላል፤ ከጉዳት ያላገገመውን የትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድንም የቀኝ ተመላላሽ ቦታን ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ተከላካዩ ጆ ጎሜዝ ያገግማል ተብሎ ከተጠበቀበት አሳልፎ የካቲት መጨረሻ ብቁ ይሆናል ተብሏል፡፡ የመሀል ተከላካዩ ደያን ሎቭረን በቋንጃ ጉዳት አሁንም ከጨዋታ ውጭ ነው፡፡
የዌስት ሃም አሰልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሪኒ ለቀድሞ ክለቤ ማንችስተር ሲቲ ስል፤ የቀያዮቹን ሩጫ በምሽቱ ለማስቆም እሰራለሁ ብለዋል፡፡
‹‹ማሸነፍ የምንችል ከሆነ መጀመሪያ ለክለቤ ደስተኛ እሆናለሁ፤ ከዚያ በእኛ ማሸነፍ ለማንችስተር ሲቲ በር የሚከፍት ከሆነ የእኛ ችግር አይሆንም፤ በርግጥ የማንችስተር ሲቲ ደጋፊ ነኝ፤ መሪዎቹን ለማስቆም ግን ጥሩ አቅም ያስፈልጋል›› በማለት ተናግረዋል፡፡
የቀያዮቹ አለቃ የርገን ክሎፕ ደግሞ ‹‹ሁሌም የምናደርገውን ዛሬም እንሰራለን፤ ያለንበትን ሁናቴ በራሳችን መንገድ አንቆጣጠረዋለን ራሳችንንም አዘጋጅተናል፤ ከሌሎች ሰዎች የሚመጣን ተፅዕኖ አንቀበልም›› ብለዋል፡፡
ማንችስተር ሲቲ ትናንት ምሽት አርሰናልን በአጉዌሮ ሶስት ግቦች 3 ለ 1 ረትቶ፤ ከሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 2 ነጥብ ዝቅ አድርጓል፡፡ ዛሬ ሊቨርፑሎች ድል የሚያርጉ ከሆነ ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት የሚመለስ ይሆናል፡፡
በሁለቱ ቡድኖች የባለፉት አራት ግጥሚያዎች ቀያዮቹ አራቱንም በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈዋል፡፡
ሊቨርፑል በሊጉ 61 ነጥቦችን በመያዝ ይመራል፤ ሲቲ በ59 ይከተላል፤ ቶተንሃም በ57 ሶስተኛ፣ ቼልሲ በ50 አራተኛ ደረጃን ይዘዋል፤ ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ደግሞ በ48 እና 47 ነጥቦች አምስተኛና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ሳላህ ከፍተኛ ግብ አስቆጣነቱን በ16 ጎሎች እየመራ ይገኛል፡፡