መጋቢት 29 ይጀመራል የተባለው አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ
መጋቢት 29 ይጀመራል የተባለው አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራዉ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ይጀመራል ተብሎ ዕቅድ የተያዘለት አራተኛዉ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ወስኗል፡፡
ኮሚሽኑ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ በመጨረሻም አራተኛውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ማድረጉን የሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል፡፡
ኮሚሽኑ በጉዳዩ ላይ መክሮ እልባት ላይ ለመድረስ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ የሚታወስ ሲሆን በቆጠራ ሂደቱ ላይ የተነሱ ጉዳዮች ወደ መግባባት እስኪደረስባቸው ድረስ ከተያዘለት ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ ይራዘም ብሏል።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ለቆጠራ ሂደቱ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ለክልሎች ዞኖችና ወረዳዎች በሚያከፋፍልበት ወቅት የገጠሙ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ነው ኮሚሽኑ ለስብሰባ የተቀመጠው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የደቡብ ክልል ባለስልጣናት ለፌዴራል መንግስት ባሳወቁት መሰረት በክልሉ በተለይ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ቆጠራውን ማካሄድ አዳጋች ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም መንግስት ወደ ክልሎች የሚሰራጨውን የቆጠራ ቁሳቁሶች እንዲቆሙ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል ብቻ የቆጠራ ቁሳቁሶችን ሙሉ ለሙሉ ማሰራጨት የተቻለው ፡፡
ለስልጠና የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችም የኮሚሽኑን ውሳኔ ተከትሎ ከየክልሎቹ እንዲሰበሰቡ ኤጀንሲው የወሰነ ሲሆን አዲሱን የቆጠራ ጊዜ በተመለከተ ኮሚሽኑ ይፋ ያደርጋል መባሉን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡