ሱዳን ከዓለም ዓቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አይ ሲ ሲ ጋር በጦር ወንጀሎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማማች፡፡
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 18፣ 2012 ሱዳን ከዓለም ዓቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አይ ሲ ሲ ጋር በጦር ወንጀሎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማማች፡፡ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሃምዶክ ዓለም ዓቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሱዳን ዳርፉር ተከስቶ በነበረው ግጭት የጦር ወንጀሎችንና የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የፈጸሙትን አካላት ለፍርድ ለማቅረብ በሚደረገው ሂደት በትብብር እንሰራለን ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር መንግስታቸው ከአይ ሲ ሲ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረው በጦር ወንጀለኝነት፣ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ አስከፊ ወንጀሎችንና በገዛ ወገናቸው ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙ አካላትን በአፋጣኝ ለፍርድ እንዲቀርቡ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡
እንደ አሶሺየትድ ፕረስ ዘገባ የሱዳን ባለስልጣናት የቀድሞ የሀገሪቱ መሪ የነበሩት ኦማር አል በሽር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳርፉር ላይ በተፈጸመው የጦር ወንጀሎችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ክስ ይመሰረትባቸው ዘንድ ተላልፎ እንዲሰጡ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2003 በሱዳን ዳፉር ተከስቶ በነበረው ግጭት ሶስት መቶ ሺህ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ቀዬያቸውን ጥለው መሰደዳቸው ይታወሳል፡፡