በአዲስ አበባ ከተማ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የ28 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
አርትስ 14/01/2011 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ በመዲናዋ ባንዲራ ከመስቀል እንዲሁም ከሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት ጋር ተያይዘው በተነሱ ግጭቶች የሰው ህይወት ማለፉን በኮልፌ ክፍለ ከተማ የ14፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 5፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ 1፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 3፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 5 በድምሩ የ28 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል።
ከእነዚህም ወስጥ የአብዛኛዎቹ ህይወት ያለፈው በድብደባ፣ በድንጋይ እና በዱላ ሲሆን የ7 ሰዎች ህይወት ደግሞ በፀጥታ ሀይሎች እንዳለፈ ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
በፀጥታ ሀይሉ ህይወታቸው ካለፉ ዜጎች መሃከል አንድ ሰው በፖሊስ ስህተት የሞተ ሲሆን፥ ይህን የፈፀመው ፖሊስም በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሁከቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩ 1 ሺህ 204 የሚሆኑ ግለሰቦችን ከተለያዩ አካባቢዎች በመሰብሰብ በቀጣይ ሌላ ጥፋት ላይ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ሰንዳፋ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ለተሃድሶ ስልጠና ወደ ጦላይ እንዲገቡ መደረጉንም ተናግረዋል።