በአፍሪካ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን ማለፉ ተሰማ::
አዲስ አበባ፣ ህዳር 09፣ 2013 በአፍሪካ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን ማለፉ ተሰማ:: ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ እንዳስታወቀው በአሁኑ ጊዜ በአህጉሩ በወረርሽኙ የተያዙ ሰወች ከ1 ሚሊዮን 986 ሺህ በላይ ደርሰዋል፡፡ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 47 ሺህ 647 መድረሱን የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከለያና መቆጣጠሪያ ማእከል በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
ሲ ጂ ቲ ኤን እንደዘገበው በበሽታው ከተያዙት ሰዎች መካከል ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ማገገማቸው ታውቋል፡፡ ዜጎቻቸው በበሽታው በብዛት ከተጠቁባቸው ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ግብፅና ኢትዮጵያ በመጀመሪያዎቹ ረድፍ ላይገኛሉ፡፡ አህጉሩ በየቀጠናው ተከፋፍሎ ሲታይ ደግሞ ደቡባዊ አፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን የሰሜኑ የአፍሪካ ክፍል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ነው የተባለው፡፡
የአፍሪካ ሀገራት የጤና ፖሊሲ ከቀሪው ዓለም ጋር ሲነፃፀር አናሳ መሆኑን ተከትሎ በቫይረሱ ይበልጥ ይጠቃሉ የሚለው ቅድመ ግምት ከፍ ብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ግን ውጤቱ ከትንበያው የተራራቀ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በየጊዜው በሚያወጣቸው የማንቂያ መልእክቶች ግን አፍሪካ ከሁሉም የበለጠ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ አህጉር መሆኑን ሳይጠቅስ አያልፍም፡፡