loading
በኢትዮጵያ ፍትህ እንዲረጋገጥ ብዙ ስራዎች ይቀራሉ-ኢ.ሰ.መ.ኮ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ለሰብአዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡ ጥሪው የቀረበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የ10 ወር የሥራ  ክንውን ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትሕ እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች  ቋሚ  ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ባለፉት 10 ወራት ግጭት የተከሰተባቸው 65 ቦታዎችን መድረሱን፣ ባለፉት 3 ወራት ብቻ 450 ሺህ ስደተኞችን የሚያስጠልሉ አስር ስደተኛ ካምፖች ላይ የክትትል ሥራ ማከናወኑን ተናግሯል፡፡


በአምስት ክልሎች የሚገኙ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ገደማ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚያስጠልሉ 47 ጊዜያዊ  መጠለያዎችና ተቀባይ ማኅበረሰቦችን  መጎብኘቱን እና ሪፖርት እና ምክረ ሃሳቦችን እንደየአግባብነቱ በይፋዊ መግለጫ ወይም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካሎች ማቅረቡም ተገልጿል። ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች አያያዝን በተመለከተ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 82 ማረሚያ ቤቶች እና በ270 ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማከናወኑንም ከተጠቀሱት የክትትልና
የምርመራ ሥራዎች መካከል ናቸው።


ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነትና በሌሎች አካባቢዎች ከብሔር ማንነትና ከሃይማኖት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በሚያገረሹ ግጭቶች ሳቢያ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ እጅግ በርካታ ሰዎች ለሞት፣ ለአካልና ለሥነ ልቦና ጉዳት፣  ለመፈናቀልና ለንብረት ውድመት  መዳረጋቸውን  አስረድተዋል። በመሰረተ ልማቶች ላይ በደረሰ ውድመትም መሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን፣  ከፍተኛና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውንና ሁኔታው በስጋትነት እንደቀጠለ አስታውሰዋል፡፡


በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አፋርና አማራ ክልል ተስፋፍቶ የነበረው ጦርነት አሁን ላይ መብረዱና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መሻሻሉ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ፣ ፍትሕ እንዲረጋገጥ ገና ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ መግለጻቸውን ኮሚሽኑ ለአርትስ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *