በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደደቢት ከሊጉ መሰናበቱን ሲያረጋግጥ፤ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሀግብር ጨዋታዎች፤ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በአዲስ አበባ እና ክልል ስታዲየሞች ላይ ተካሂደዋል፡፡
ትናንት አዲስ አበባ ላይ የምስራቁን ድሬዳዋ ከነማ ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ለ 0 ድል በማድረግ ወደ ድል ጎዳና መመለስ ችሏል፡፡ ፈረሰኞቹ መረብ ላይ ያሳረፏቸው ሁለት ግቦች በተከላካይ መስመር ተሰላፊው አስቻለው ግርማ የፍፁም ቅጣት ምት ጎሎች ተገኝተዋል፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ ሪቻርድ አርተር በድሬዳዋው በረከት ሳሙኤል ተጠልፎ የተገኘችውን አስቻለው አስቆጥሮ ቡድኑን በ15ኛው ደቂቃ ላይ መሪ አድርጓል፡፡
ሁለተኛዋ ግብ በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተገኘች ሲሆን 70ኛው ደቂቃ አካባቢ አብዱልከሪም ወደ ግብ ያሻማት ኳስ በድሬዳዋው የተከላካይ መስመር ተሰላፊ አንተነህ ተስፋዬ ዕጅ ተነክታለች ተብላ በዕለቱ ዳኞች የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቷል፤ የድሬዳዋ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ውሳኔውን ቢቃወሙም የቅዱስ ጊዮርጊስ አስቻለው ግርማ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሮ ቡድኑ አሸናፊ ሆኗል፡፡
ሙሉ ጨዋታው ላይ አልፎ አልፎ ከሚደረጉ የግብ እንቅስቃሴዎች እና ሙከራዎች ውጭ ሳቢ ያልነበረ፤ የኳስ ቅብብሎሹ በተሎ የሚጨናገፍ፤ በአጠቃላይ የተቀዛቀዘ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ስቱዋርት ሃልን ካሰናበተ በኋላ በዘሪሁን ሸንገታ እየተመራ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል፤ በዚህም ቡድኑ 43 ነጥቦችን በመሰብሰብ አራተኛ ደረጃን አሁንም ይዟል፡፡
ክልል ላይ አዳማ ከተማ በሜዳው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ደደቢትን 4 ለ 0 በመርታት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ሸኝቶታል፡፡ ወደ ባህር ዳር ያቀናው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያለግብ በአቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡
ወደ ትግራይ ክልል የተጓዘው መከላከያ ሽረ ላይ በስሑል ሽረ የ2 ለ 1 ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ የሽረው ቡድን ድል ማድረጉን ተከትሎ ከጦሩ ቡድን በግብ ክፍያ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ በ26 ነጥብ ከወራጅ ቀጠና በአንድ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡
ቅዳሜ ዕለተ በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ተጫውተው የመጀመሪያውን አጋማሽ ያለግብ በአቻ ውጤት አጠናቅቀው፤ ሁለተኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በዝናብ ምክንያት ያላከናወኑት ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ትናንት ረፋድ ላይ ቢሾፍቱ ላይ ተጫውተው በዚያው የአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡
የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ወደ ሶዶ አምርቶ በወላይታ ድቻ 2 ለ 1 ተረትቶ ተመልሷል፡፡ መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ ከሜዳው ውጭ በጅማ አባ ጅፋር 2 ለ 0 መመራት ተነስቶ ሁለት አቻ በመለያየት አንድ ነጥብ ወደ መቐለ ይዞ መመለስ ችሏል፡፡
በደቡብ ደርቢ ሲዳማ ቡና በሃዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ደቡብ ፖሊስን ከመመራት ተነስቶ በ4 ለ 2 ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡
ፕሪምየር ሊጉን ፋሲል ከነማ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ሲዳማ ቡና አንገት ለአንገት ተያይዘው በዕኩል 49 ነጥቦች ባላቸው የግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ1- 3 ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመቐለ እና አዲስ ግደይ ከሲዳማ በ15 ጎሎች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመሩ ይገኛል፡፡