በደቡብ አፍሪካ የስደተኛ ጠልነት ችግር አሁንም የማይጠፋ አዙሪት ሆኖ ቀጥሏል ተባለ::
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2013 በደቡብ አፍሪካ የስደተኛ ጠልነት ችግር አሁንም የማይጠፋ አዙሪት ሆኖ ቀጥሏል ተባለ:: በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች በሀገሬው ተወላጆች የሚደርስባቸው ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉ እንዳሳሰበው ሂውማን ራይትስ ዋች የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ገልጿል፡፡
ድርጅቱ ከአፍሪካ እና ከእስያ ተሰደው በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ሰዎች በየትኛውም ጊዜ የመጤ ጠሎቹ ኢላማዎች መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
አፍሪካ ኒውስ በዘገባው እንዳስነበበው የደቡብ አፍሪካ የህግ አስከባሪ አካላት ስደተኞቹን ከጥቃት ከመጠበቅ አኳያ የሚያሳዩት ቸልተኝነት ሁኔታውን አባብሶታል፡፡
ስደተኞቹ ለፍተው ያፈሩትን ንብረት ማጣት ብቻ ሳይሆን እስከ ህይዎት ህልፈት የሚያደርስ አካላዊ ጥቃት እየደረሰባቸው በመሆኑ የሀገሪቱ መንገስት ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል ድርጅቱ፡፡ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ከአሁን ቀደም የተፈፀመውን ተመሳሳይ ድርጊት ተከትሎ ለስደተኞቹ አስፈላጊውን ጥበቃ አደርጋለሁ ቢልም ችግሩ አሁንም እንዳልተፈታ ነው የሚነገረው፡፡ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2008 ስደተኛ ጠል የሚባሉት የሀገሬው ተወላጆች ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 62 ስደተኞች መገደላቸው ይታወቃል፡፡