በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተመረቀ::
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተመረቀ:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት የተመረቀው ማዕከሉ ቀድሞ በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በአምስት እጥፍ እንደሚያሳድገው ተነግሯል፡፡ ይህም ለኩላሊት ህመምተኞች እፎይታን ይሰጣል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማዕከሉን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ባዩት ነገር በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘመናዊ ብቁ የጤና ተቋማት በመገንባት ተመጣጣኝና ፍትሀዊ የጤና አገልግሎትን ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የኩላሊት ህመም የጤና ስርዓቱን እየፈተነ ያለ ህመም በመሆኑ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ገቢ የሌላቸውንና አነስተኛ ገቢ
ያላቸውን ዜጎች በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች የነፃ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም እንደ አዲስ ሲዋቀር ከተሰጠው ተልእኮ ውስጥ አንዱ የጤና ስራ ማስፋፋት መሆኑን ገልፀው አሁን ተስፋ ሰጪ ነገሮችን ማየት መቻላቸውን ነው ከንቲባዋ የገለጹት፡፡ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ በአጋርነት መስራት አስፈላጊነት ታምኖበት ህጋዊ ማዕቀፍ ወጥቶለት እየተተገበረ መሆኑንም ጠቁመዋል።