በጋምቤላ ክልል በሰለጠነ ባለሙያ የወለዱ እናቶች ሽፋን 40 በመቶ መሆኑ ተገለፀ::
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 23፣ 2013 በጋምቤላ ክልል በሰለጠነ ባለሙያ የወለዱ እናቶች ሽፋን 40 በመቶ መሆኑ ተገለፀ:: በክልሉ የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ጤናና የስርዓተ ምግብ ሁኔታን ለማሻሻል ያለመ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል፡፡ በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት በክልሉ በሰለጠነ ባለሙያ
የሚወልዱ እናቶች ሽፋን 40 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሚኒስትሯ የህጻናት ክትባት መሻሻል ቢታይበትም አሁንም ዝቅተኛ ሽፋን እንዳለው አንስተዋል፡፡ የህጻናት መቀንጨርን ከመቀነስ ጋር በተያያዘ በክልሉ አበረታች ውጤት መመዝገቡን በመጥቀስ ችግሩ አሁንም የተቀናጀ ጥረትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ጤናና የስርዓተ ምግብ ሁኔታን ይበልጥ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡በሀገሪቱ የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለማሻሻል እንዲሁም የመላውን ህብረተሰብ የጤና አገልግሎትና ተደራሽነት ለማስፋት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ተብሏል፡፡ የሀይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው መንግስት ባለፉት 20 ዓመታት የእናቶችንና ህፃናትን ጤና፣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ የሥርዓተ-ምግብ ሁኔታን ለማሻሻል ፖሊሲ ቀርፆ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ስራዎች ካስገኟቸው ውጤቶች መካከልም ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት ሞትና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የሚከሰት የእናቶች ሞት መቀነስ ተጠቃሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መረጃውን ያገኘነው ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ነው፡፡