በጋምቤላ ክልል በአራት ወረዳዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት አስታወቀ።
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 በጋምቤላ ክልል በአራት ወረዳዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት አስታወቀ።
የጎርፍ አደጋው የተከሰተው በክልሉ ደጋማው አካባቢ ሲሆን የአደጋው ተጠቂዎች በላሬ፣ መኮይ ዋንቱዋ እና ኢታንግ በተባሉ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ቀበሌዎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን በጎርፍ አደጋው ሳቢያ የተፈናቀሉትን ነዋሪዎች ለጊዜው ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች እንዲጠለሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በአደጋው ምክንያት በኢታንግ ልዩ ወረዳ 2 ሺህ 40፣ በላሬ ወረዳ 1 ሺህ፣ በዋንቱዋ ወረዳ 619 እንዲሁም በመኮይ 480 ዜጎች ተፈናቅለዋል ነው ያሉት ሀላፊው፡፡
አቶ ጋትቤል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መግለጻቸውን ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው የጎርፍ አደጋው ሲከሰት ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች ላይ መጠለላቸውን ጠቅሰው ከመንግስት በኩል አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡