በፊፋ የወንዶች ብሄራዊ ቡድን ወርሀዊ የደረጃ ሰንጠራዥ ዋልያዎቹ 150ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል
አርትስ ስፖርት 15/02/2011
የፊፋ ኮካኮላ የጥቅምት ወር የደረጃ ሰንጠራዥ ዛሬ ይፋ የሆነ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ካለፈው ወር አንድ ደረጃ ዝቅ በማለት በ1054 ነጥብ፤ 150ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፤ በካፍ ዞንደግሞ 44ኛ ደረጃ ላይ ተገኝቷል፡፡ በአጠቃላይ የወሩ የደረጃ ሰንጠራዥ ቤልጅየም በ1733 ነጥብ ስትመራው፣ ፈረንሳይ በ1732 ነጥብ ሁለተኛ፣ ብራዚል 1669 ነጥብ ሶስተኛ ሲቀመጡ ክሮሺያና እንግሊዝአራተኛና አምስተኛ ደረጃ ላይ ተገኝተዋል፤ ዩሯጓይ፣ ፖርቹጋል፣ ሲውዘርላንድ፣ ስፔንና ዴንማርክ ከአምስት አስከ አስር ያለውን ደረጃ ተቆናጥጠዋል፡፡ በካፍ ዞን ደግሞ ቱኒዚያ በ1515 ነጥብ ቀዳሚ ስትሆንከአለም 22ኛ፣ ሴኔጋል በ1501 ሁለተኛ ከአለም ደግሞ 25ኛ ስትሆን፤ ናይጀሪያ በ1431 ነጥብ ከአፍሪካ ሶስተኛ ከአለም 44ኛ እንዲሁም ዲ.ሪ ኮንጎ ከአፍሪካ አምስተኛ ከአለም 46ኛ በመሆን ተቀምጠዋል፡፡በወሩ ጅብራላተር፣ ናሚቢያና ዚምባብዌ ጥሩ ደረጃ ያሻሻሉ ሲሆን፤ በአንፃሩ ሞዛምቢክ፣ ሰሜን አየርላንድ እና ዲ.ሪ ኮንጎ በቁጥር ከፍ ያለ ደረጃዎችን አሽቆልቁለዋል፡፡