loading
በፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት አዲስ አበባ ገቡ

አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል።

ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ የገባው የአርበኞች ግንቦት 7 ልኡክ በድርጅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የድርጅቱ ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመምራት ነው አዲስ አበባ የገባው።

የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮችና አባላቶች አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታዎች ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካህሱና አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ጨምሮ ሌሎች ከፍኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም አርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች እና አባላቶች ደማቅ አቀባበል በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የድርጅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫም፥ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት በመምጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሀገር ወስጥ ቆይታቸውም በአሁኑ ወቅት እየመጣ ያለው ለውጥ ቀጣይነት አንዲኖረው ከመንግስት፣ ከሲቪክ ማህበራት እና የህብረተሱ ጋር ሰፋፊ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አክለውም፥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ድርጅታቸው ከማንኛውም የፖለቲካ ሀይል ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑንም አንስተዋል።

ቀጣይ ስራቸውን አስመልክቶም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፥ “ቅድሚያ ሰጥተን የምንሰራው ስራ አሁን በተገኘው ምቹ ሁኔታ ሀገሪቱን በጋራ ሆነን እንዴት ወደ ተረጋጋ የዴሞክራሲ ስርዓት እንወስዳታለን የሚለውን ነው” ብለዋል።

አሁን እየመጣ ያለው ለውጥ በሀገሪቱ ብሩህ ተስፋ እንዲታይ አድርጓል ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ ይህንን ለውጥ የማስቀጠል ስራም ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም ብለዋል።

ስለዚህ ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች በተለይም ህብረተሰቡ በሰከነ መንፈስ አሁን የተገኘውን ለውጥ የማስጠበቅ ሚናውን መወጣት አለበት ሲሉም መልእከት አስተላልፈዋል።

አርበኞች ግንቦት 7 እስከአሁን ለውጡ የሄደበትን ርቀት በማጤን በሀገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል በማድረግ የተጀምረው የለውጥ ሂደት ወደ እውነተኛ ዘላቂ ለውጥ ለመሸጋገር የሚያስችል ሁኔታ አለ የሚል ድምዳሜ ላይ
በመድረሱ ነው ወደ ሀገር የገባው።

አርበኞች ግንቦት 7 ከዚህ ቀደም በኤርትራ ያለውን ወታደራዊ ካምፕ መዝጋቱ የሚታወስ ነው፡፡

መንግስት በውጭ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ስምምነት ላይ መድረሱ ተከትሎ በውጭ ሀገራት የሚንቀሳቀሱ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ መወሰናቸው ይታወሳል።

ከእነዚህ ውስጥ አርበኞች ግንቦት 7 ጨምሮ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ እና ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ተጠቃሽ ናቸው።

መንግስትም ነፍጥ አንግበው የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱበትን፣ ከህረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉብትንና ዘላቂ ኑሮ እንዲመሩ ለማስቻልም በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ውስጥ የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሟል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *