loading
በ43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ሽኝት ተደረገ

በመጪው ቅዳሜ በዴንማርኳ አርሁስ ከተማ ለሚካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ ኢትዮጵያ በ28 አትሌቶች ትወከላለች፡፡

በስድስት እና አስር ኪሎ ሜትር ሴቶች፤ በስምንት እና አስር ኪሎ ሜትር ወንዶች እንዲሁም ድብልቅ ሪሌ የሚፎካከሩ አትሌቶች፤ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ለማውለብለብ ብርዳማውን የአውሮፓ ፀባይ እና ተፎካካሪዎቻቸውን ድል ለማድረግ በአራራት ሆቴል ከትመው ከ45 ቀናት ባለፈ ጊዜ ልምምዳቸውን ሲያከናውኑ ሰነባብተዋል፡፡

ትናንት ምሽት በአራራት ሆቴል በነበረው የሽኝት ዝግጅት፤ የአትሌቶቹ ዋና አሰልጣኝ ዋና ሱፐር ኢንተንዴንት ሁሴን ሼቦ ቡድኑ በቂ ዝግጅት እንደነበረው አስታውቀዋል፡፡

ዋና አሰልጣኙ ቡድኑ በጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኝ እና ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚጠብቅ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የልኡኩ መሪ ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ከጃንሜዳ አገር አቋራጭ ማግስት አትሌቶች ተመርጠው አስፈላጊው ዝግጅት እንደተደረገ ተናግራለች፡፡

አትሌት ደራርቱ ዴንማርክ ላይ ያለውን የአየር ፀባይ እና የቦታውን አስቸጋሪነት በቴክኒክ ክፍሉ በኩል ለአትሌቶች ማብራሪያ ተሰጥቷልም ብላለች፡፡

በውድድሩ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ወጣት እና አዋቂ አትሌቶች በዝግጅታቸው ወቅት ከአሰልጣኞቻቸው በቂ ስልጠና እንደተሰጣቸውና ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፉተናግረዋል፡፡

አትሌቶቹ በአርሁሱ ውድድርም የሀገራቸውን ስም እና ሰንደቅ ከፍ ለማድረግ ጥረታቸውን እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦለምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ መንግስት፤ ኦለምፒክ ኮሚቴው እና ፌዴሬሽኑ በኦለምፒክ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች በሚሊዮኖች ለመሸለም ተዘጋጅቷል፤ ከአሁንም ዝግጁ ሁኑ ሲሉ አበረታትተዋል፡፡

ልዑካን ቡድኑ ዛሬ ምሽት ወደ ዴንማርክ የሚያቀና ይሆናል፡፡

በዓለም አገር አቋራጭ ታሪክ ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1981 9ኛው በስፔን ማድሪድ ከተካሄደው ውድድር አንስቶ መሳተፍ የጀመረች ሲሆን በ34 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና 100 ወርቅ፣ 105 ብር እና 59 ነሃስ በአጠቃላይ በ264 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም ኬንያን ትከተላለች፡፡  

ከሜዳሊያዎቹ መካከል በሴቶች አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ 14 እንዲሁም በወንዶች አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ16 ወርቅ ቀዳሚ ናቸው፡፡

ዘንድሮም ከቀናት በኋላ በሚካሄደው ሻምፒዮና፤ ስኬት በኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ይመዘገብ ዘንዳ የቀድሞ ስመጥር ባለታሪክ አትሌቶች ለአትሌቶች ተወካዮች የአደራ ሰንደቅ ዓላማ ርክክብ ተደርጎ ታሪካቸውን እንደሚያስቀጥሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *