ቡርኪናፋሶ ወታደራዊ አቃቤ ህግ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓወሬ በ30 ዓመት እስር እዲቀጡ ጠየቀ፡፡
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ አቃቤ ህግ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓወሬ በ30 ዓመት እስር እዲቀጡ ጠየቀ፡፡ ኮምፓወሬ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው ከሳቸው በፊት ሀገሪቱን ሲመሩ በነበሩት ፕሬዚዳንት ቶማስ ሳናካራ ግድያ እጃቸው አለበት ተብለው ነው፡፡ አፍሪካ ኒውስ እንደ ዘገበው እንደ አወሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1987 አብዮታዊው መሪ ቶማስ ሳንካራ መገደላቸውን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት ኮምፓወሬ ግድያውን ከጀርባ ሆነው እንዳቀነባበሩት
ይነገራል፡፡
የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ አቃቤ ህግ ክሱን የጀመረው የፈረንሳይ ባለስልጣናት የሳንካራን ግድያ በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ይፋ ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡ አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ኮምፓወሬ በመንግስት ደህንነት ላይ ጥቃት በመሰንዘር፣ በነፍስ ግድያና አስከሬን በመደበቅ ወንጀል 12 ባልደረቦቻቸውን በስውር ሲረዱ እንደነበር አብራርቷል፡፡
ሟቹን ፕሬዚዳንት ቶማስ ሳንካራን ተክተው ስልጣኑን የተቆናጠጡት ኮምፓወሬ ሀገሪቱን ለ27 ዓመታ ያህል ያስተዳደሩ ሲሆን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 በተቀሰቀሰ ህዝባዊ አመጽ ወደ ጎረቤት ኮትዲቯር ተሰደው ለመኖር ተገደዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓወሬ የጥበቃ አዛዥ የነበሩት ሃያሲንቴ ካፋንዶ በነበራቸው የወንጀል ተሳትፎ ከአለቃቸው አኩል በ30 ዓመት እዲቀጡም አቃቤ ህግ ጠይቋል፡፡