ባለፉት ስምንት ዓመታት በመላው ሀገሪቱ ከ130 ሺህ በላይ ሰዎች በተሸከርካሪ አደጋ ጉዳት እንደደረሰባቸዉ ተገለፀ፡፡
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 15፣ 2012 ባለፉት ስምንት ዓመታት በመላው ሀገሪቱ ከ130 ሺህ በላይ ሰዎች በተሸከርካሪ አደጋ ጉዳት እንደደረሰባቸዉ ተገለፀ፡፡የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ለአርትስ በላከዉ መግለጫጉዳት ከደረሰባቸዉ ዉስጥም ካሳ የተከፈላቸው ቁጥር ከ 25ሺ እንደማይበልጥ ገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ የመንገድ ትራፊክ አደጋ በየዓመቱ ከ 4 ሺህ በላይ ሞትና ከ 15 ሺህ በላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም በንብረትም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ውድመት የሚደርስ ሲሆን ፤ከ 2005 እስከ 2012 ዓ/ም ድረስ በደረሰው አደጋ በሞት፣ በአካል ጉዳትና በተመላላሽ ህክምና ካሳ ያገኙ ተጎጂዎች መጠን ከ 19 በመቶ እንደማይበልጥ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ወቅት 3ኛ ወገን የመድን ሽፋን ባላቸው ተሽከርካሪዎች ለደረሰ ለ10, ሺህ 115 የሞትና ከ 11 ሺ በላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከ 357 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ እንደተከፈለ ታውቋል፡፡ ኤጀንሲው የቀጣይ 10 ዓመት መሪ ዕቅዱን በገመገመበት ወቅት እንደተገለጸው ባለፉት ስምንት ዓመታት ባልታወቁና 3ኛ ወገን የመድን ሽፋን በሌላቸው ተሸከርካሪዎች ጉዳት ለደረሰባቸው 388 ተጎጂዎች ከ 10ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ ከፍሏል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ በደረሱ የተሸከርካሪ አደጋዎች ለ10ሺህ387 የሞትና 12 ሺህ ከባድና ቀላል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ካሳ የተከፈለ ቢሆንም ከደረሰው አደጋ አንጻር ሲለካ በኤጀንሲውና በኢንሹራንስ ኩባያዎች ካሳ ያገኙ ሰዎች 22 ሺህ 515 ብቻ ናቸዉ፡፡
ከኤጀንሲው ዋና ዋና ስራዎች ውስጥ ሁሉም ተሽከርካሪዎች 3ኛ ወገን የመድን ሽፋን እንዲኖራቸው ማድረግ የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች በመንግስትም ሆነ በግል የጤና ተቋማት እስከ 2 ሺህ ብር በሚደርስ ወጪ አስቸኳይ ህክምና በነጻ እንዲያገኙ ማድረግ ሲሆን የ2012 ዓ/ም አፈጻጸሙ ከ3ኛ ወገን የመድን ሽፋን አንጻር 86 በመቶ እንዲሁም የተሽከርካሪ አደጋ አስቸኳይ ህክምና ተደራሽነት 37 በመቶ መሆኑን ኤጀንሲዉ ገልጿል፡፡