loading
አማራ ክልላዊ መንግስት በክልሉ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ታቅደው የሚደረጉ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አለኝ አለ

የአማራ ክልላዊ መንግስት በክልሉ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ታቅደው የሚደረጉ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አለኝ አለ

የክልሉ መንግስት ይህን ያለው በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ ነው፡፡

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ በሰጡት መግለጫ በአብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች የተሻለ ሰላም እና መረጋጋት ቢኖርም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን የሰላም መደፍረስ ጎልቶ ይስተዋላል ብለዋል፡፡

በተለይም በምዕራብ ጎንደር ዞን በተከሰተው የጸጥታ ችግር የሰዎች ህይወት አልፏል፤ከፍተኛ አካላዊ፣ማህበራዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶችም ደርሰዋል ብለዋል  ዳይሬክተሩ፡፡

ከአሁን ቀደም በሌሎች አካላት የሚደገፉ ጥቂት ግለሰቦች በፈጠሩት ሴራ  የተቀሰቀሰው የጸጥታ ችግር በሀገር ሽማግሌዎች እና በጸጥታ መዋቅሩ ጥረት ቢረጋጋም  ባለፉት ሁለት እና ሶስት ቀናት ችግሩ አገርሽቷል ብለዋል አቶ አሰማኸኝ፡፡

አቶ አሰማኸኝ እንዳሉት በተለይ ‹‹ሽንፋ›› አካባቢ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ያስከተለው ጉዳት ታቅዶ የተሰራ እና በስልጠና  የታገዘ እንደሆነ ይታመናል ነው ያሉት፡፡የፌደራል እና የክልል የጸጥታ አስከባሪ ግብረ ኃይል ወደ ቦታው አቅንቶ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑንም አቶ አሰማኸኝ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

አቶ አሰማኸኝ በመግለጫቸው ህብረተሰቡ ሰላሙን ለማስከበር ከመንግስት ጎን መቆም እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ዘገባው የአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ነው፡፡

 

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *