ኢትዮጵያን ለመቀየር ሰማይ መቧጠጥ አይጠበቅብንም – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 አዲስ ለተዋቀረው የካቢኔ ከፍተኛ አመራሮች በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ስልጠና መስጠት ተጀመረ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጠናው ሲጀምር በሰጡት የሥራ መመሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ አቧራ ለብሰውና ቋጥኝ ተጭኗቸው የሚገኙ በርካታ ሀብቶችን አውጥቶ ለጥቅም ማብቃት የአመራሩ ተልዕኮ ነው ብለዋል። እነዚህን ሀብቶች አውጥቶ በመጠቀም አገራችንንን ለመቀየር ሰማይ መቧጠጥ አይጠበቅብንም ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የዓላማ ጽናት ስንላበስ ጫና፣ ግፊት እና መከራ የኢትዮጵያን ብልጽግና በር የሚከፍቱ እንጂ የሚያዳፍኑ አይደሉም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያገለግሉትንና የሚገለገሉበትን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስልጣን ላይ ስንቀመጥ ሰው መሆናችንን ሳንረሳ አሻራ ለማስቀመጥ ተግተን ከሰራን ውጤት ከደጃችን ነው ብለዋል። የስልጠናው ዓላማም ማሳወቅ፣ ማነሳሳት፣ ለቡድን ሥራ ማዘጋጀትና ውጤታማ ማድረግ እንደሆነ
አስታውቀዋል። ዘገባው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ነው፡፡