ኢትዮጵያ ክብሯን ለመድፈር የሚቅበዘበዙትን አደብ የሚያስገዙ ጀግኖች አጥታ አታውቅም ሲሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ገለጹ።
አዲስ አበባ፣መስከረም 11 2014 ሚንስትሯ ኢንጂኔር አይሻ መሀመድ ይህን ያሉት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በ2013 ዓ.ም በጀት የእቅድ አፈጻጸምና የ2014 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ ከውይይቱ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ ከተሞች የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት ዘመቻን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ አስጀምረዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀገሩ አምባሳደርና ጠበቃ በመሆን የአገራችንን ዕውነት ለዓለም የሚያሳዩበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን" ብለዋል ኢንጂኔር አይሻ። ለዓለም አቅፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውንት ከምናሳውቅባቸው መንገድች አንዱ የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት ዘመቻ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ከተሞች ዘመቻውን በይፋ መቀላቀላቸውን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ የሽንፈት ታሪክ የሌላትና ከክብሯን ዝቅ ሊያደርጓት የሚባዝኑትን ሁሉ አደብ የሚያስገዙ ጀግኖች አጥታ የማታውቅ ታላቅ አገር ናት" ብለዋል ሚኒስትሯ።
ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማዳከም የሚሯሯጡ ጠላቶቿ ህብረት ፈጥረው አገሪቷ እንዳታድግና እንዳትለማ እየሰሩ መሆናቸው ገሃድ የወጣ እውነት መሆኑንም አብራርተዋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ፈተናዎች በድል ተውጥታ ወደ ሚመጥናት ከፍታ የጀመረችውን ጉዞ እንደምትቀጥል ምንም የሚያጠራጥር ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸዋል። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊትና ለሕልውና ዘመቻው እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡