loading
ኢትዮ-ቴሌኮም የአዲስ አበባ የኔትወርክ ጥራት ችግር በ3 ወራት ውስጥ ይፈታል አለ

ኢትዮ-ቴሌኮም የአዲስ አበባ የኔትወርክ ጥራት ችግር በ3 ወራት ውስጥ ይፈታል አለ

አርትስ 19/04/2011
በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የሚታየውን የኔትወርክ ጥራት መጓደል በሶስት ወራት ውስጥ መፍታት የሚያስችል የኔትወርክ ማስፋፊያ ስራ እያከናወነ መሆኑን ኢትዮ-ቴሌኮም አስታወቀ፡፡
መርካቶን ጨምሮ ቦሌ አራብሳ፣ ኃይሌ ጋርመንት፣ ጀሞና፣ ቦሌ አካባቢዎችና በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ቦታዎች የሞባይል ኔትወርክና የኢንተርኔት አገልግሎት ጥራት መጓደል በስፋት ይስተዋላል፡፡
በእነዚህ ቦታዎች ያለውን የኔትወርክ ጥራት መጓደል በአጭር ጊዜ ለመፍታት ኢትዮ-ቴሌኮም ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ በመስሪያ ቤቱ የኔትወርክ ዲቪዥን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ኃይለመስቀል  ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡
የኔትወርክ ችግሩም የተከሰተው በዋናነት በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና በቦታው ያለው ኔትወርክ በመጨናነቁ ነው ብለዋል፡፡
በእነዚህ ቦታዎች ያለውን የኔትወርክ አቅም ለመጨመር የሚስችሉ ዕቃዎች ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ በዚህ ሳምንት መግባታቸውንምአቶ ቴዎድሮስ ገልፀዋል ፡፡
በመዲናዋ በተመረጡ ቦታዎች ጥቅም ላይ የሚውሉት ዕቃዎቹ የኔትወርክ ጥራት ችግሩን ከመፍታት ባለፈ ተጨማሪ 500 ሺህ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም አላቸው ብለዋል፡፡
የኔትወርክ ማስፋፊያው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በሁለት ወር ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ችግሩ እንደሚፈታ ተመልክቷል፡፡
ይህ የመፍትሄ ውጥን በፊትም አሁንም ኔትወርክ በሌለባቸው ቦታዎች መፍትሄ የሚሰጥ ሳይሆን የኔትወርክ ጥራት መጓደል በሚታይባቸው ቦታዎች ማሻሻያዎችን ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በዘላቂነት የሞባይል ኔትወርክና የኢንተርኔት አገልግሎት የመቆራረጥ ችግርን ለመፍታት የኔትወርክ አቅምን ከመጨመር ባለፈ አማራጭ የኤሌክትሪክ ሀይልን ለመጠቀም እተየሰራ እንደሆነም ኢትዮ-ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *