ኤርዶሀን በአንካራ በተካሄደው ምርጫ ከተማዋን ለመምራት የሚስያችል ድምፅ ሳያገኙ ቀሩ፡፡
ኤርዶሀን በአንካራ በተካሄደው ምርጫ ከተማዋን ለመምራት የሚስያችል ድምፅ ሳያገኙ ቀሩ፡፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሀን በሀገሪቱ በተደረገ የአካባቢ ምርጫ በዋና ከተማዋ አንካራ እና በሌሎችም ከተሞች በተቃዋሚዎቻቸው ተሸንፈዋል፡፡
አንካራን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በተደረጉ የአካባቢ እና የከንቲባ ምርጫዎች መንሱር ያቫስ 50.6 በመቶ ድምፅ በማግኘት በኤርዶሀን ላይ ድልን ተቀዳጂተዋል፡፡
ሚድል ኢስት ሞኒተር እንደዘገበው በአንካራ በለስ የቀናቸው ያቫስ እና ያልተጠበቀ ሽንፈት የገጠማቸው ኤርዶሀን በኢስታንቡል ከተማ በየፊናቸው ምርጫውን አሽንፈናል እያሉ ነው፡፡
የአንካራው ውጤት እንደሚያሳየው የኤርዶሀን ፓርቲ ከ40 በመቶ በታች የሆነ የመራጮችን ድምፅ ነው ያገኘው፡፡
ኤርዶሀን ስለውጤቱ ሲናገሩም ይህ ለኛ ጥሩ ትምህርት ነው ፤ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2023 ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጠንካራ ስራዎችን እንድንሰራ ያነሳሳናል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፓርቲያቸው በርካታ ከተሞችን በዚህ ምርጫ ቢያጣም ወደፊት የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ገቢራዊ በማድረግ በዋናው ምርጫ ጥሩ ተፎካካሪ እንደሚሆን አረጋግጠዋል፡፡
ህዝባችን ለውጥ እንደሚፈልግ በግልፅ አሳይቶናል፤ ከዚህ በኋላ የቤት ስራችንን በአግባቡ በመስራት መራጮቻችንን ወደኛ መመለስ ይገባናል ያሉት ኤርዶሀን ለዚህም እንቅስቃሴያችን የሚጀምረው ዛሬ ነው ብለዋል፡፡
መንገሻ ዓለሙ