loading
ከ90 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ እያስመዘገበ ያለው ውጤት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ።

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 ከ90 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ እያስመዘገበ ያለው ውጤት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ። ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም ያላትን ሃብት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሏ ውጤታማ እንዳልሆነችና በርካታ የቆዳ ውጤቶችን ከውጭ እንደምታስገባ ተነግሯል፡፡


በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ሌሎች ችግሮች ለኢንዱስትሪው የገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት መሆኑን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡ አሁን ላይ ችግሩን ለመቋቋም ከውጭ የሚገቡ የቆዳ ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የአምራች ኢንዱስትሪውን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነውም ተብሏል፡፡


የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዳኛቸው ሽፈራው ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባውን የቆዳ ውጤት በአገር ውስጥ ለመተካት የአምራች ኢንዱስትሪውን አቅምና ጥራት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።በኢትዮጵያ በህጋዊም ሆነ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የቆዳ ምርት ወደ
አገር ውስጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡


በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት የቆዳና ሌጦ ውጤቶች በአገር ውስጥ ገበያ በስፋት በማምረት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን እየተሰራ ነው ብለዋል። ይህን ችግር ለማቃለል የተለያዩ ስራዎች እየተተገበሩ መሆኑን ጠቅሰው ከሚሰሩት ስራዎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምንና ጥራትን ማሳደግ ዋነኛው ነው ብለዋል።
በአገር ውስጥ የተማሪዎችንና የመከላከያ ሰራዊት ጫማዎችንና ቦርሳዎችን በስፋትና በጥራት ማቅረብ መጀመሩንም ነው አቶ ዳኛቸው የተናገሩት። የቆዳና ሌጦ ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለአገሪቱ ጥሩ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲያመጣ ዘርፉን በስልጠና፣ በፋይናንስና በተለያዩ ዘርፎች መደገፍ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *