ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አዲሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የካቢኔ አወቃቀር እያደነቁ ነው
ዶክተር አብይ አዲሱን ካቢኔ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማፅደቃቸውን ተከትሎ አለም አቀፍ
መገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ምልከታዎቻቸውን ይዘው ወጥተዋል።
ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ንግግር ዋቢ በማድረግ በዘገባዉ እንዳለው ሴቶች
ሚኒስትሮች መሾማቸው በኢትዮዽያ ማህበረሰብ ለዘመናት ነግሶ የቆየውን ሴቶች መምራት አይችሉም
የሚል ብሂል ታሪክ የሚያደርጉበት ዕድል ፈጥሯል ብሏል ፡፡
ጋዜጣው በብሪታኒያ የከል ዩኒቨርሲቲ የኢትዮዽያ ጉዳይ ኤክስፐርት አዎል አሎን በመጥቀስ እንደዘገበው
የፆታ እኩልነት አለመኖር ተንሰራፍቶባት በቆየችውና የወንዶች የበላይነት በነገሰባት ሃገር ይህን መሰል
የሴቶች ተሳትፎ እኩል የሆነበት የካቢኔ አወቃቀር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው ብሏል።
ሜይል ኦን ላይን በበኩሉ የኢትዮዽያ አዲሱ ካቢኔ 50 በመቶ ሴቶችን ወደ ሃላፊነት በማምጣት
ማስተዋወቁንና በሃገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋን ሴት መከላከያ ሚኒስትር መሾሙን አድንቋል።
የቱርኩ አናዶሉ ዜና ወኪል በበኩሉ በተለይ በቁጥር እኩል ሴቶችን ያቀፈው ካቢኔ ከሙስና የፀዳና
ውጤታማ ስራዎችን እንዲያከናውን በሚል መዋቀሩንና ለዚሁ እንዲያግዝም 28 የነበሩት የሚኒስቴር
መስሪያ ቤቶችም ቁጥር ወደ 20 ዝቅ እንዲሉ መደረጉን ዘግቧል።
ኢትዮዽያ በሃገሪቱ በየአካባቢው የሚታየውን ግጭት መፍትሄ የሚፈልግለት ‘የሰላም ሚኒስቴር’
የተሰኘ አዲስ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማቋቋሟን በዘገባው የዳሰሰው ደግሞ ሮይተርስ ነው።