የሃይሌ ማናስ አካዳሚ የ2ኛ ደረጃ አዳሪ ት/ቤት የመጀመሪያ ተማሪዎቹን ተቀበለ::
አዲስ አበባ፣ጥር 04፣ 2013 የሃይሌ ማናስ አካዳሚ የ2ኛ ደረጃ አዳሪ ት/ቤት የመጀመሪያ ተማሪዎቹን ተቀበለ:: የሃይሌ- ማናስ አካዳሚ ውጤት የሆነው ይህ አዲስ ጥራቱን የጠበቀ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ት/ቤት በደብረ ብርሃን ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የ9ኛ ክፍል ተማሪዎቹን
ተቀብሏል፡፡ በአዲሱ ካምፓስ ወላጆች በአካል ተገኝተው ልጆቻቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን የጉብኝት እና የኮቪድ-19
የጥንቃቄ መመሪያ ገለፃ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
አካዳሚው 22 ሴቶች እና 16 ወንዶች የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን የተቀበለ ሲሆን ከአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ ደብረ ብርሃን እና ሌሎች ከተሞች የተወጣጡ መሆናቸውን ለአርትስ የተላከው መግለጫ ያመላክታል፡፡ ት/ቤቱ መስከረም 2020 ስራውን ይጀምራል ተብሎ የተነገረ ቢሆንም በተቀሰቀሰው ወረርሽኝ እና ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መውሰድ የሚገባቸው በመሆኑ እንዲራዘም ሆኗል ተብሏል፡፡ በተለይ ወረርሽኙ ትምህርት ቤቱ በያዘው ዕቅድ ልክ እንዳይሰራ የገደበው መሆኑን የተናገረ ሲሆን በቀጣይ ዓመታት አካዳሚው በእያንዳንዱ የ2ኛ ደረጃ የክፍል ደረጃ 100 ተማሪዎችን በመቀበል
በአጠቃላይ 400 ተማሪዎችን አስተናግዳለሁ ብሏል፡፡
የሃይሌ- ማናስ አካዳሚ በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ርብቃ ሃይሌ እና ባለቤቷ ጂን ማናስ በአሜሪካ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሆኖ የተመሰረተ ሲሆን በትህርታቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ኢትዮያውያን ተማሪዎችን ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ማስቻል ዓላማው እንደሆነ ተነግሯል፡፡