loading
የማሊ ወታደራዊ መንግስት ለተቃጣበት መፈንቅለ መንግስት ምዕራባዊያንን ወቀሰ፡፡

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 የማሊ ወታደራዊ መንግስት ለተቃጣበት መፈንቅለ መንግስት ምዕራባዊያንን ወቀሰ፡፡ ራሱ በመፈንቅለ መንግስ ስልጣን የያዘው የኮሎኔል አሲሚ ጎይታ አስተዳደር የተቃጣበትን መልሶ ግልበጣ የጸጥታ ሃይሎች እንዳከሸፉት ገልጿል፡፡ የአሁኑ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2020 ወዲህ ሁለት መፈንቅለ መንግስት ላስተናገደችው ማሊ ፖለቲካዊ ትኩሳቷ እንዳይበርድ ያደርጋል የሚል ስጋት ፈጥሯል ነው
የተባለው፡፡


ወታደራዊ መንግስቱ በመግለጫው ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ጀርባ ከምእራባዊያኑ ሀገራት የአንዱ እጅ አለበት ብሏል፡፡ የየትኛው ሀገር መንግስት ይህን ሴራ እንደደገፈ በስም ያልጠቀሰው መግለጫው ድርጊቱን አጥብቆ እደሚያወግዝ ነው ያብራራው፡፡ የፖለቲካ አዋቂዎች ግን የሻከረውን ግንኙነታቸውን ለአብነት በመጥቀስ ከመፈንቅለ መንግስቱ ጀርባ በደፈናው የምትጠረጠረው ሀገር ፈረንሳይ እንደምትሆን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡


በፓሪስና በባማኮ መካከል የተፈጠረው ውጥረት በኮሎኔል አሲሚ ጎይታ መንግስት ላይ የምእራባዊያን ጫና እንዲበረታ አድርጎታል ነው የሚባለው፡፡ የቀድሞዋ የማሊ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ ከ9 ዓመታት በላይ ጂሃዲስቶችን ለመዋጋት ከቆየችባት ሀገር ወታደሮቿን እንድታስወጣ ቀጭን ትዕዛዝ እንደተሰጣት ይታወሳል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *