የምስራቅ ሐረርጌ አገረ ስብከት የመስቀል በዓል የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን በመተግበር እንደሚያከብር አስታወቀ::
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 የምስራቅ ሐረርጌ አገረ ስብከት የመስቀል በዓል የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን በመተግበር እንደሚያከብር አስታወቀ::
በሐረሪ ክልል የደመራና የመስቀል በዓልን ሐይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በአንድነትና እርስ በርስ በመደጋገፍ በጥንቃቄ እንደሚከበር ነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት የገለፀው።
የምስቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት የትምህርትና ስልጠና ክፍል ሃላፊ መልዓከ ሰላም ታደለ ፊጣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር፣ የሚያጎለብትና በዩኔስኮ የተመዘገበውን የመስቀልና የደመራ በዓል በሰላም እና በአንድነት እናከብረዋለን ብለዋል፡፡ በዓሉን ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ሀገር ዜጎች የሚታደሙበትና የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ለሌሎች የሚያሳይ ደማቅ በዓል በመሆኑ ምዕመናኑ ለአገር በሚበጅ ሁኔታ እራሳቸውን ከኮሮና በሽታ በመጠበቅ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ህዝበ ክርስትያኑ ባዓሉን ሲያከብር በመደጋገፍና በመረዳዳት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው ቤተክርስቲያንም በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከክልሉ መስተዳድር አካላት ጋር የተለያዩ ዝግጅቶችን ማደረጉን አመልክተዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በዓሉ ያለ አንዳች ጸጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር አስፈላጊ ዝግጅት
መደረጉን ገልጿል። ለዚህም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በተለይም በክልሉ ከሚገኙ የፀጥታ መዋቅሮች ጋር የጋር እቅድ ከማዘጋጀት ባለፈ የሀይማኖት አባቶችን በማወያየት አብሮ በመስራት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ሰላምን ለመጠበቅ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተገንዝቦ ያለ ስጋት እራሱን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት በመጠበቅ በዓሉን እንዲያከብር መክረዋል።