የሳይበር ጥቃቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይችላሉ -የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት
አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 25፣2014 በሕዳሴው ግድብ እና በከፍተኛ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች መክሸፋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለጸ። የሀገሪቱን ሰላም እና ዕድገት በማይፈልጉ ሀገራት የሚደገፍ ድርጅት የሕዳሴው ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል በማቀድ ‘ብላክ ፒራሚድ ዎር’ በሚል ስያሜ የሳይበር ጦርነት መክፈቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ተናግረዋል። የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሙባቸው እና እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ 37 ሺህ ኮምፒውተሮች ላይ ጥቃት በመፈጸም የሕዳሴው ግድብን ለማስተጓጎል እንደተሞከረም ገልጸዋል።
ጥቃቶቹም በኢንፎርሜሽን ደህንነት አስተዳደር ጥብቅ ክትትል ምንም ጉዳት ሳያስከትሉ እንዲቋረጡ እና እንዲመክኑ መደረጋቸውን አስታውቀዋል። የሕዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጨት ከጀመረ በኋላ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚችል ይገመታል ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፣ ከዚህ በኋላም የሳይበር ምኅዳሩን በመጠቀም ግድቡ በአግባቡ ኃይል እንዳያመነጭ እና እንዲቆም ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።
ለዚህም ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ተግባራዊ በማድረግ ከሕዳሴው ግድብ ግንባታ እና ቁጥጥር ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ግድቡን በተመለከተ ከአመራረት እስከ ግንባታ ዕቃዎች ማጓጓዣ የሚያጠቃልሉ ሥራዎች ላይ የሳይበር ምኅዳሩን በመጠቀም ከፍተኛ ክትትል ይደረጋልም ብለዋል። በሕዳሴው ግድብ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶች እስካሁን ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያደርሱ እንዲመክኑ ቢደረግም አሁንም የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች እየተሰነዘሩ መሆኑን አስታውቀዋል። የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ሁልጊዜም አንድ እርምጃ ቀድሞ ማየት፣ ማቀድ እና መተግበር ያስፈልጋል ማለታቸውን የኢትጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ ያመለክታል።