የትግራይ ክልል የድህነት መጠንን በየዓመቱ በ2 በመቶ ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል አሉ ዶ/ር ደብረፂዮን
አርትስ 10/02/2011
የትግራይ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባዔውን በዛሬው እለት ማካሄድ ጀምሯል።
በምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ የ2011 በጀት ዓመት እቅድን ያቀረቡት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፥ የትግራይ የድህነት መጠን በየዓመቱ በ2 በመቶ ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በክልሉ በከተማ እና በገጠር የሚኖረው ህብረተሰብ ኢኮኖሚውን በማሳደግ የድህነት መጠኑን ከ17 በመቶ በታች ለማውረድ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ለዚህም በግብርና እና ጥቃቅንና አነስተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ዶ/ር ደብረፅዮን፥ በክልሉ እስካሁን የነበረውን የህዝብ ብዛት መሰረት ያደረገ አደረጃጀት ዳግም ለመፈተሽ የሚያስችል ጥናት እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
ለዚህም እንደማሳያ የተለያየ የሀብት መጠን ያላቸው ተመሳሳይ አደረጃጀት እንዲኖራቸው የተደረጉት የመንግስት መዋቅሮች ማስተካከያ እንደሚደረግባቸው አስታውቀዋል።
የወረዳዎች እና ቀበሌዎች አደረጃጀት ላይም ማስተካከያ እንደሚደረግባቸውም ነው ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ዶክተር ደብረፂዮን የገለጹት።
ዶክተር ደብረፅዮን አክለውም፥ ምሁራን ያቀረቡትን ምክረ ሀሳብ መሰረት በማድረግ በክልሉ ሶስት የልማት ኮሪደሮች እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ዶክተር ደብረፅዮን ለምክር ቤቱ ያብራሩት።
የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እየሆነ ያለው የመሬት አስተዳደር አሰራር እንደሚፈተሽ እና ማስተካከያ እንደሚደረግበት የገለጹት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፥ የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ ከቀበሌ ጀምሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
እንዲሁም በቀበሌ ያለው የመሬት ዳኝነት እንዲፈርስ እና አደረጃጀታቸው እንዲቀየር እና በቀበሌ ደረጃ ያሉ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት እንደሚስተካከልም አስታውቀዋል።
በሲቪል ሰርቪስ የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጮች የሆነ ቢሮክራሲን ለማስተካከል ጥናት እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
የመንግስት ሰራተኞችን አቅም በመፈተሽ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል ሲቪል ሰርቫንቱ በስልጠና እና በምዘና እንዲያልፍ ይደረጋልም ብለዋል።
የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው እንዲያብብ ሲቪል ማህበራት ከማንኛውም አካል ጫና ነጻ እንዲሆኑ ጥረት እንደሚደረግም ነው ዶክተር ደብረፅዮን ያስታወቁት።
በትግራይ ክልል በርካታ መልካም አስተዳደር ችግር እና ልማትን ጨምሮ በርካታ ችግሮች እንዳሉ የገለጹት ዶክተር ደብረፅዮን፥ ችግሮቹን ለመቅረፍ በየደረጃው ያለው አስፈፃሚ አካል ከፍተኛ ስራ መስራት እንደሚጠበቅበት በአፅንዎት ገልጸዋል።
በ2011 ዓ.ም ለሪፎርም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ምክትል ርእሰ መስተዳደሩ ባቀረቡት እቅድ እና አቅጣጫ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ኤፍ.ቢ.ሲ