የናይጄሪያ ታጣቂ ቡድኖች አግተዋቸው የነበሩት 53 ሰዎችን ለቀቁ::
አዲስ አበባ፣የካቲት 16፣ 2013 የናይጄሪያ ታጣቂ ቡድኖች አግተዋቸው የነበሩት 53 ሰዎችን ለቀቁ:: የሀገሪቱ ባለስልጣናት በሰጡት ማረጋገጫ ኒጀር ውስጥ በታጣቂዎቹ በእገታ ስር ከነበሩ ሰዎች መካከል 20 ሴቶችንና 9 ህፃናትን ጨምሮ 53ቱም ተለቀዋል፡፡ ሰዎቹ በታጣቂዎቹ ታፍነው የተወሰዱት ባለፈው ሳምንት በአውቶቡስ በሚጓዙበት ወቅት እንደነበር ተነግሯል፡፡
የኒጄር መንግስት ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ ታጋቾቹ በተቻለ ፍጥነት እንዲለቀቁ አስፈላጊው ድርድር ተደርጓል ብለዋል፡፡ ከእገታ የተለቀቁት ሰዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ ሁሉም አስፈላጊው የህክምና ምርመራ እንደተደረገላቸውም ቃል አቀባይዋ አክለው ገልፀዋል፡፡ ባለፈው እሁድ አጋቾቹ አሉበት የተባለውን ስፍራ ለማሰስና ለማስለቀቅ ተሰማርቶ የነበረ አውሮፕላን ተከስክሶ ሰባት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ በቀጠናው የሥጋት ቦታዎች ተብለው በተለዩ አካባቢዎች በርካታ ወታደሮች ቢሰማሩም በየቀኑ በሚባል ደረጃ ተማሪዎች ሲታገቱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡