የአርንጓዴው ጎርፍ ልኡካን ሽልማት ተበረከተለት
በ43ኛው የዴንማርክ አርሑስ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ተሳትፎ በአምስት ወርቅ፣ በሶስት ብር እና በሶስት ነሐስ በአጠቃላይ 11 ሜዳሊያዎች ከዓለም እና ከአፍሪቃ ቀዳሚውን ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቶች (አረንጓዴው ጎርፍ) እና ልዑክ በአራራት ሆቴል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን አመራሮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አመራሮች፣ የቀድሞ ውጤታማ አትሌቶች እና ሌሎች በተገኙበት አቀባበል እና ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
ለልዑካን ቡድን ከእንግዶች በኩል የአበባ ጉንጉን እና የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡
በተገኘው ውጤት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ዳግም በአለም ፊት ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አበርክቶ ለነበራቸው ምስጋና እና ክብር በተሰጠበት ውሎ ከተለያዩ ተቋማት ለውጤታማው ቡድን የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል፡፡
አትሌቶች በቀጣይ በሚኖሩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ በማድረግ ሀገራቸውን ከዚህ በላቀ እንዲያስጠሩ በተሻለ መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም አስፈላጊው ትብብር ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች በኩል እንደሚቀርብ ተገልጧል፡፡
ለቡድኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 647 ሺ ብር፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 315 ሺ ብር እንዲሁም የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ስፖርት ኮሚሽን ለአትሌቶች እንዳስመዘገቡት ስኬት ልክ በተናጠል እና በቡድን ሽልማት ሲሰጥ፤ ለቡድን መሪዎች፤ አሰልጣኞች፤ የህክምና ባለሙያዎች እና ሌሎች ልኡካን እንደየ ሃላፊነታቸው የገንዘብ ሽልማቱ ተሰጥቷል፡፡
እስካሁን በተደረጉ 43 የዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች ኢትዮጵያ በ35 ውድድሮች ተካፍላ፤ 105 ወርቅ፣ 108 ብር እና 62 ነሐስ በአጠቃላይ 275 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች፡፡