የአንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራሉ
ሊጠናቀቅ የሰባት ሳምንታት ዕድሜ የቀረው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የሳምንቱ መርሃግብር ጨዋታዎች ዛሬን ጨምሮ ነገ እና ከነገ በስቲያ ቀጥለው ይካሄዳሉ፡፡
በብሬንዳን ሮጀርስ የሚመራው ሌስተር ሲቲ ኪንግ ፓወር ላይ በራፋኤል ቤኒቲዝ የሚሰለጥነውን ኒውካስትል ዩናይትድ ያስተናዳል፡፡ ጨዋታው ዛሬ ምሽት 4፡00 ላይ ይጀመራል፡፡
በነገው ዕለት ስድስት ያህል ፍልሚያዎች ሲካሄዱ 9፡ 30 ሲል ቶተንሃም ሆተስፐር በሜዳው ከሊጉ የወረደውን ሀደርስፊልድ ታውን ይገጥማል ፡፡ አዲሱ ስታዲየም ለስፐርሶች ገድ ይዞ የመጣ ይመስላል፤ ክለቡ በተከታታይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በድል መወጣት ችሏል፡፡
ምሽት 12፡00 ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ብራይትን በአሜክስ ከቦርንመዝ፤ በርንሊ በቱርፍ ሞር ከ ካርዲፍ ሲቲ፤ ፉልሃም በክሬቨን ኮቴጅ ከኢቨርተን እንዲሁም ሳውዛምፕተን በሴንት ሜሪ ከወልቭስ ይጫወታሉ፡፡
ምሽት 2፡30 ላይ ከአንድ እስከ አራት ያለው ደረጃ ላይ ለማጠናቀቅ ትግል ውስጥ ያለው ማንችስተር ዩናይትድ በኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም ከዌስት ሃም ዩናይትድ ጋር ይገናኛል፡፡
መጠነኛ ተስፋ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር መጠነኛ ተስፋ አድርገው የነበሩት ቀያይ ሰይጣኖቹ በቀጣዩ ዓመት የውድድሩ ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ ከአንድ እስከ አራት ማጠናቀቅ ግድ ይላቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቀሪ የሊጉ ጨዋታዎች በወጥነት አሸናፊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
እሁድ ሁለት ግጥሚያዎች ሲደረጉ፤ ለሻምፒዮንነት እየተፎካከሩ የሚገኙት ቡድኖች ተጠባቂ ግጥሚያ ይከውናሉ፡፡
ማንችስተር ሲቲ ወደ ለንደን አቅንቶ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ሲጫወት ከሮይ ሁድሰን ቡድን ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡ ጨዋታው 11፡05 ላይ በሴል ኽረስት ፓርክ ስታዲየም ይከናወናል፡፡
በዕለቱ ምሽት 1፡30 ሲል የመርሲ ሳይዱ ሊቨርፑል አንፊልድ ላይ የሳምንቱን ተጠባቂ ፍልሚያ ከቼልሲ ጋር ያደርጋል፡፡
የማውሪዚዮ ሳሪው ቼልሲ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት የቻምፒዮንስ ሊግ መድረክ ተሳታፊ ለመሆን ሁለት አማራጮች ያላቸው ሲሆን የዩሮፓ ሊጉ ሻምፒዮን መሆን አሊያ ሌላኛው በሊጉ ከአንድ እስከ አራት ደረጃ ውስጥ ማጠናቀቅ ነው፡፡
እናም ሰማያዊዎቹ በዚህ ጨዋታ ከቀያዮቹ ጋር ለህልውናቸው ሲሉ አሸናፊ ሁነው ለመውጣት ይሰራሉ፡፡
በየርገን ክሎፕ የሚሰለጥኑት ሊቨርፑሎች ለሶስት አስርት ዓመት በተጣጋ ዕድሜ ዋንጫውን ወደ ቤታቸው ለማምጣት የለፉ ሲሆን ዘንድሮን ተስፋ አድርገዋል፡፡ የዚህ ጨዋታ ውጤት ደግሞ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡
ሰኞ አርሰናል በቪካሬጅ ከዋትፎርድ ጋር ይገናኛል፡፡