የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የጀርመን-አፍሪካ 2021 ሽልማት አሸናፊ ሆኑ፡፡
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2014 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የጀርመን-አፍሪካ 2021 ሽልማት አሸናፊ ሆኑ፡፡ ኢሰመኮ ለአርትስ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የጀርመን-አፍሪካ ፋውንዴሽን (DAS) ዛሬ መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የሽልማቱን እጩዎችን የሚያወዳድረው ኮሚቴ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በጀርመን አገር በአይነቱ ከፍተኛ ለሆነው ሽልማት ሲመርጣቸው በሙሉ ድምጽ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ሽልማቱ ዋና ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እንዲሰፍን ለሚደረገው ጥረት ላበረከቱት የሕይወት ዘመን አስተዋጽዖ እውቅና የሚሰጥ እንደሆነ አሳውቋል። በተጨማሪም፣ የፋውንዴሽኑ መግለጫ ሽልማቱ ዶ/ር ዳንኤል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በከፍተኛ ደረጃ እንዲለወጥና ገለልተኝነቱ እንዲረጋገጥ፣ እንዲሁም ሥልጣንና ኃላፊነቱ እንዲሰፋ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና እውቅና የሚሰጥ መሆኑን አክሎ ገልጿል። ይፋዊ የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ በእ.ኤ.አ. ኅዳር 2021 የሚካሄድ ይሆናል። ከ25 ዓመታት በላይ በየዓመቱ ሲካሄድ የቆየው ይህ ሽልማት፣ በሙያቸው የላቀ አመራር ላሳዩና ለእድገትና ለመሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አፍሪካውያን የሚሰጥ ነው።