የእግር ኳስ ዳኛው አስገራሚ የታገቢኛለሽ ጥያቄ ይሁንታን አግኝቷል
ነገሩ እንዲህ ነው ባለፈው ሳምንት በአውሮፓዊቷ ሀገር ሮማኒያ የአራተኛ ዲቪዚዮን ሲ.ኤ ኦርዲያ እና ሲ.ኤስ ዲዮስጅ በተባሉ ሁለት ክለቦች መካከል የእግር ኳስ ጨዋታ ሊካሄድ፤ ከጨዋታው በፊት የሚደረገው ሂደት እየተከናወነ ባለበት ወቅት ከስታዲየሙ መሀል መስመር ትንሽ ፈቀቅ ብሎ፤ የ22 ዓመቱ ረዳት አርቢትር ማሪዩስ ማቲካ በጨዋታው በሀላፊነት ለነበረችው ፍቅረኛው የ20 ዓመቷ ረዳት አርቢትር ጂዮርጂ ዱማ በርከክ ብሎ የታገቢኛለሽ ጥያቄ ያቀርባል፡፡
እንደ ኢ.ኤስ.ፒ.ኤን ዘገባ ቀልድ ቢጤ ሲያክልበት፤ የእሺታ መልሱ ውሳኔ ወደ ቪዲዮ አሲስታንት ሪፈሪ/ቫር ( ይህ ማለት በምስል የታገዘ የእግር ኳስ ዳኝነት ውሳኔ ነው) አመራ ነገር ግን ምስጋና ይግባና ይሄንን አስገራሚ እና የልብ ወዳጇን የጋብቻ ጥያቄ አርቢትር ዱማ በፍቅር እየተፍነከነከች ‹‹እሺ አገባሃለሁ›› ስትል ምላሿን ሰጠች ፡፡
ይህ ያልተጠበቀ ክስተት ሲሆን የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች የሚሆነውን ሁሉ ተመልካቾች ነበሩ፡፡ እነርሱም አፀፋውን ሰጡ ጥንዶቹ የፍቅር እና የደስታ ህይወት እንዲመሩ እየተመኙ በጭብጨባ አጀቧቸው፡፡
ከአካባቢው በወጡ መረጃዎች ሁለቱ ጥንዶች ላለፉት ሶስት ዓመታት በፍቅር ጓደኝነት የኖሩ ሲሆን በሰሜን ምዕራብ ሮማኒያ ቢሆር ከተማ በመስመር ዳኝነት ያገለግላሉ፡፡
‹‹ ጭራሽ አልጠበኩም ነበር›› ብላለች ጆርጂ ዱማ ለቢሆር ኦንላይን ስትናገር ‹‹ ወጣ ያለ ድንገቴ ፣ አስቂኝ አስገራሚ ክስተት ነው›› ስትል አክላለች፡፡
ስተቱን የታደሙ እና የሰሙ ሰዎች የሳምንቱ ገራሚ ታሪክ ሲሉ አውደሰውታል፡፡