የዩሮ 2020 የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ይደረጋሉ
በዛሬው ዕለት ሶስት ምድቦች ላይ የሚገኙ ሀገራት የማጣሪያ ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ፡፡
ምድብ አንድ ላይ በአሰልጣኝ ጋሪዝ ሳውዝጌት የምትመራው እንግሊዝ በዊምብሌይ ስታዲየም ቼክ ሪፐብሊክን ምሽት 4፡45 ላይ ታስተናግዳለች፡፡
የሊቨርፑሉ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ዕረቡ ዕለት የጀርባ ህመም ያጋጠመው ሲሆን አሁን ደግሞ የማንችስተር ዩናይትዱ ማርከስ ራሽፈርድ በቁርጭምጭሚት ጉዳት የዛሬውን ጨዋታ ከሞንቴኔግሮ ጋር የሚከናወነው ግጥሚያ ሊያልፈው እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ከሶስቱ አናብስት ስብስብ ውስጥ ከዚህ ቀደም የአማካዮቹን ፋቢያን ደልፍ እና ሩበን ሎፍተስ ቺክ እንዲሁም ተከላካዮች ጆን ስቶንስ እና ሉክ ሾው ከጨዋታ ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ እንግሊዛውያኑ ባለፉት 18 የዬሮ የማጣሪያ ጨዋታዎች ያልተሸነፉ ሲሆን በ15ቱ ደግሞ የበላይነታቸውን አሳይተዋል፡፡
እዚሁ ምድብ ምሽት 2፡00 ቡልጋሪያ ከ ሞንቴኔግሮ ይጫወታሉ፡፡
በሁለተኛው ምድብ ደግሞ በተመሳሳይ ሰዓት ፖርቱጋል በስታዲዮ ዳ ሉዝ ዩክሬንን በመግጠም የዩሮ ማጣሪያዋን ትጀምራለች፡፡
የፖርቱጋሉ አምበል ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከሩሲያው የዓለም ዋንጫ በኋላ ዛሬ ምሽት የመጀመሪያ ጨዋታውን ለሀገሩ ያደርጋል፡፡
በአሰልጣኝ ፈርናንዶ ሳንቶ በኩል ዦሴ ፎንቴ እና ጆ ሞቲንሆ በድጋሚ ጥሪ የደረሳቸው ሲሆን ለቤኒፊካ የሚጫወተው ወጣቱ ጆ ፍሊክስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሩን እንዲያገለግል ቡድኑን ተቀላቅሏል፡፡
እዚሁ ምድብ ላይ ሉክሰምበርግ ከ ሊቱኒያ ጋር ይጫወታሉ፡፡
በምድብ ስምንት ደግሞ የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ባለ ድል የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ከሞልዶቫ አቻው ጋር ቺሲኑ ላይ በዚምብሩ ስታዲየም ይጫወታል፡፡
አይምሪክ ላፖርትን እና አሌክሳንደር ላካዜትን በስብስቡ ያላካተተው ብሔራዊ ቡድን፤ የኦስማን ዴምቤሌን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም ተብሏል፤ የባየርን ሙኒኩ ኪንግስሊ ኮማን ግን ከ2017 በኋላ ወደ ቡድኑ ተመልሷል፡፡
አልባኒያ ከ ቱርክ እንዲሁም አንዶራ ከ አይስላንድ ከምድቡ የሚከናወኑት ሌሎች ጨዋታዎች ናቸው፡፡