loading
የፖፕ ሙዚ አቀንቃኙና ፖለቲከኛው ሮበርት ኪያጉላኒ መታሰሩን ተከትሎ በዩጋንዳ አመፅ ተቀስቅሷል::

አዲስ አበባ፣ ህዳር 11፣ 2013 የፖፕ ሙዚ አቀንቃኙና ፖለቲከኛው ሮበርት ኪያጉላኒ መታሰሩን ተከትሎ በዩጋንዳ አመፅ ተቀስቅሷል:: በቅፅል ስሙ ቦቢ ዋን በመባል የሚታወቀው ዩጋንዳዊው ፖለቲከኛን መታሰር ለመቃወም አደባባይ በወጡ ደጋፊዎችና የፀትታ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት 7 ሰዎች መሞታቸውም ተሰምቷል፡፡
አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት ሰዎች መካከል ከ40 በላይ የሚሆኑት የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡

ቦቢ ዋይን በዩጋንዳ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ምክንያት አንድ እጩ ተወዳዳሪ ከ200 በላይ ደጋፊዎቹን እንዳያሰባስብ የሚከለክለውን ህግ ጥሶ ተገኘ በሚል ሰበብ ነው የታሰረው፡፡ ቦቢ ዋይን ወደ ፖለቲካው ዓለም ከገባ ጀምሮ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ፕሬዚዳንት ዌሪ ሙሴቬኒን አጥብቆ በመተቸት ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ በዩጋንዳ ፖሊስ በተደጋጋሚ ተይዞ እስርና እንግልት ሲደርስበት እንደቆየም ይነገራል፡፡

በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ለመሳተፍ የተመዘገቡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ለጊዜው የምርጫ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ መታገዳቸውን ዜናው አክሎ አስታውቋል፡፡
ቦቢ ዋይን ከአሁን ቀደም በእስር ቤት በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የጤና መታወክ ገጥሞት ውጭ ሀገር ድረስ ተጎዞ ህክምና ተከታትሎ ተመልሷል፡፡ በወቅቱ የህመሙ መንስኤ የፖሊስ ድብደባ ነው ቢባልም የዩጋንዳ ፖሊስ ግን ነገሩን ሀሰት ነው በማለት ማስተባበሉ ይታወሳል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *