ደግመን ደጋግመን ለኢትዮጵያ ለመሰዋት የተዘጋጀን ነን – ሌ/ጀነራል ባጫ ደበሌ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2013 እኛ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስለ ኢትዮጵያ መናገር ሳይሆን ህይወት የሚደገም ከሆነ ደግመን ደጋግመን ለኢትዮጵያ ለመሰዋት የተዘጋጀን ነን ሲሉ ሌ/ጀነራል ባጫ ደበሌ ተናገሩ፡፡ እኛ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ስለ ኢትዮጵያ መናገር ሳይሆን ህይወት የሚደገም ከሆነ ደግመን ደጋግመን ለኢትዮጵያ ለመሰዋት የተዘጋጀን ነን ሲሉ የአገር መከላከያ የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ተናገሩ፡፡
በዛሬው እለት በሸራተን አዲስ እየተከበረ በሚገኘው የኢትዮጵያዊነት ቀን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ የጥናት ጽሁፎች በረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እና በዶ/ር ዲማ ነገዎ አማካኝነት ቀርቧል፡፡ በዝግጅቱ ላይ አምስት የውይይት አቅራቢዎች የተሳተፉ ሲሆን የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ፣ ዶ/ር ወዳጄነህ መሀረነ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዲሁም ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ በጥናት ጽሁፍ ላይ የራሳቸውን ሃሳብ ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ ኮሚሽነር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ እንዳሉት፣ ዛሬ ላይ ለመድረስ ኢትዮጵያዊነት ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል ያሉ ሲሆን ሀብት ወደ ገንዘብ ቀይሮ ቁጭትን ለመወጣት አሁን ያለው ትውልድ ታሪክ መስራት አለበት ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ኩራት እና ክብር ነው ያሉት ፖለቲከኛ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ኢትዮጵያዊነት ጌጥ አይደለም፤ የጌጦቻችን ሁሉ ማኖሪያ አምድ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ወዳጄነህ መሀረነ ማንም ግለሰብ ይሁን ቡድን ኢትዮጵያን ሊያፈርስ በድንጋይ ቢቀጠቅጣት ድንጋዩ ይፈርሳል እንጂ ኢትዮጵያ መቼም አትፈርስም ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ለቀሪዎቹ የአፍሪካ ሀገራት እንደ አልማዝ የምታበራ ሀገር ናት ሲሉም አክለዋል፡፡ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት አርበኞች፣ የኢኮኖሚ፣ የሞራል እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ስታደርግ የቆየች ሀገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለሰላም እና ደህንነት በአፍሪካ ከማንም በላይ ቀዳሚ ሀገር ናት ያሉ ሲሆን አሁን የገጠሙን ፈተናዎች ኢትዮጵያን በጽናት ለማቆየት ይረዳሉ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ቀን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በፓናል ውይይት በሸራተን እየተካሄደ ነው፡፡