loading
ፒተር ቼክ በዚህ የውድድር ዓመት ማብቂያ ግብ መጠበቄን አቆማለሁ ብሏል

የ36 ዓመቱ የቀድሞ ቼካዊ ኢንተርናሽናል ግብ ጠባቂ ፒተር ቼክ በተያዘው የውድድር ዓመት ማብቂያ ከግብ ጠባቂነቱ እንደሚገለል አስታውቋል፡፡

በቼልሲ ቤት የ11 ዓመት ቆይታ የነበረው ቼክ ወደ ለንደን ተቀናቃኝ ክለብ አርሰናል የተዛወረው በ2015 ነበር፡፡ ራሱን ግብ ከመጠበቅ ለማግለል ያወሰነበትን ጊዜ ይፋ ሲያደርግ ባደረገው ንግግር ‹‹ በፕሪምየር ሊጉ 15 ዓመታትን ተጫውቻለሁ የቻልኩትን እያንዳንዱን ክብር ተቀዳጅቻሁ፤ ማሳካት ያለብኝን ሁሉ አሳክቻሁ የሚል ስሜት ይሰማኛል›› በማለት ተናግሯል፡፡

‹‹በዚህ የውድድር ዓመት አንድ ተጨማሪ ዋንጫን ከአርሰናል ጋር ለማሳካት ጠንክሬ መስራቴንም እቀጥላለሁ›› ሲል አክሏል፡፡

ቼክ በቼልሲ ቤት በነበረበት ወቅት በ2006 ህዳር ወር ክለቡ ከሬዲንግ ጋር በነበረው ግጥሚያ ከሬዲንጉ ስቴፈን ሀንት ጋር ተጋጭቶ የእግር ኳስ ህይወቱ አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ችሎ ነበር ቢሆንም ከሶሰት ወራት ማገገም በኋላ በድጋሜ ወደ ሜዳ ተመልሷል፤ ወደ ሜዳ ሲመለስ ግን ጥቁር ኮፍያ መሳይ ጭምብል መከላከያ አጥልቆ እንዲጫወት ተገዷል፡፡

ፒተር ቼክ ‹‹በፕሮፌሽናል የተጫዋችነት ዘመኔ ይህ 20ኛ የውድድር ዘመኔ ነው፤ የመጀመሪያ የፕሮፌሽናል ፊርማዬንም ካኖርኩ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ስለዚህ ከጨዋታ ማግለል ትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ ይሰማኛል›› በማለት ገልጧል፡፡

በቀጣይም ከሜዳ ውጭ ያለ ህይወት ምን እንደሚሆን፤ ወደ የትኛውስ አቅጣጫ እንደምጓዝ እየተመለከትኩ ነው ሲል ተናግሯል፡፡

ቼክ የእንግሊዝን ምድር የረገጠው በ2004 ከፈረንሳዩ ሬን በ7 ሚሊየን ፓውንድ ሂሳብ ለቼልሲ ፊርማውን ሲያስቀምጥ ሲሆን ክፉ ደጉን ካሳለፈበት ቼልሲ ጋር አንድ የቻምፒዮንስ ሊግ እና አራት የፕሪምየር ሊግ ስኬቶችን ጨምሮ 13 ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል፡፡

የቀድሞ ክለቡ ቼልሲ እና የአሁን ክለቡ አርሰናል ለሰጣቸው ግልጋሎት ምስጋናቸውን ችረው ወደፊት መልካሙ ሁሉ እንዲገጥመው ተመኝተዋል፡፡ ከእርሱ ጋር ተጫውተው ያሳለፉ እንደ ካርሎ ኩዲችኒ፣ ቲያቡ ኩርትዋ፣ ጆን ቴሪ፣ ዲዲዬ ድሮግባ እና ሌሎች ያላቸውን ወዳጅነት በማስታወስ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *