ፕሮፌሰር መስፍንን የሚዘክር ፋውንዴሽን::
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2013 የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሥራዎችን የሚዘክር ፋውንዴሽን ሊቋቋም መሆኑ ተገለፀ፡፡
የፕሮፌሰር መስፍን የሥራ ባልደረባ የነበሩት አቶ ያሬድ ሃይለማርያም የሟቹን ሥራዎችን የሚዘከር ፋውንዴሽን እንደሚቋቋም ለኢዜአ ገልጸዋል።
ፋውንዴሽኑን የማቋቋም ሀሳብ ከህልፈተ ህይወታቸው በፊት ሲታሰብ የነበረ ጉዳይ እንደነበረ ገልጸው፣ የፕሮፌሰር መስፍን ድንገተኛ ሞት ሐሳቡን ፈጥኖ ሥራ ላይ ለማዋል አነሳሽ ሆኗል ብለዋል። ፋውንዴሽኑን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለመመስረት መታቀዱንም አቶ ያሬድ አስታውቀዋል።
ፋውንዴሽኑ በፕሮፌሰር መስፍን ሥራዎች ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት እንደሚያከናውን ገልጸዋል። ፋውንዴሽኑን ለመመስረት ኮሚቴ መቋቋሙንም ተናግረዋል። ለፋውንዴሽኑ የሚያስፈልጉ የቦታ፣የህንጻና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ ከመንግሥት ጋር ውይይት መጀመሩንም አቶ ያሬድ አስረድተዋል። መንግሥትና ህብረተሰቡ ፋውንዴሽኑን ለማቋቋም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አቶ ያሬድ ጥሪ አቅርበዋል።