የኢራንን ጉዳይ የሚመለከተውን ዓለም አቀፍ ስብሰባ ትራምፕ ሊመሩት ነው፡፡
አርትስ 30/12/2010
ሮይተርስ እንደዘገበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢራን ጉዳይ ላይ የሚመክርበትን ስብሰባ የሚመሩት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፡፡
መረጃውን ለጋዜጠኞች የተናገሩት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ ናቸው፡፡
የስብሰባው ዋና ትኩረት ኢራን ለዓለም አቀፉ ህግ ስላላት ተገዥነት ሲሆን በዚህ ወር ኒው ዮርክ ውስጥ ይካሄዳል ተብሏል፡፡
ከስብሰባው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሀኒ በስብሰባው አጀንዳ ዙሪያ ሀሳባቸውን ለምክር ቤቱ ያቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አሜሪካ ይህ ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ አጥብቃ እንደምትቃወም አምሳደር ኒኪ ሀሌይ ተናግረዋል፡፡
በድርጅቱ የሩሲያው ምክትል አምባሳደር ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ ደግሞ ስብሰባው ማተኮር ያለበት ኢራን ከመንግስታቱ ድርጅትና ከሀያላን ሀገራት ጋር በ2015 የፈረመችው እና አሜሪካ ጥላው የወጣችው የኒውክሌር ስምምነት ላይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡