loading
ጥቂት የሠራዊት አባላት ወደ ቤተ መንግስት እንዲሄዱ ከጀርባ በመሆን ሲያነሳሱ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑ ተገለፀ

አርትስ 03/02/2011

ጥቂት የሠራዊት አባላት ወደ ቤተ መንግስት እንዲሄዱ ከጀርባ በመሆን ሲያነሳሱ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን አስታወቁ።

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን በዛሬው እለት አጠቃላይ የመከላከያ ሰራዊቱን አስመልክ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ባሳለፍነው መስከረም 30 2011 ዓ.ም ጥቂት የሠራዊት አባላት የጥቅማ ጥቅም እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለማቅረብ ወደ ቤተ መንግስት የሄዱበት አካሄድ ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል።

የመልካም አስተዳደር እና ሌሎች የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ሲገባቸው በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ማቅረብ እንፈልጋለን በሚል ወደ ቤተ መንግስት መሄዳቸው ስህተት መሆኑንም አክለዋል።

ተግባራቸውም ህገ መንግስቱን የጣሰ እና ከወታደራዊ ስነ ምግባር ያፈነገጠ መሆኑን ነው ጀነራል ሰዓረ በመግለጫቸው ያስታወቁት። 

በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላትም በተግባሩ መጸጸታቸውን እና ይቅርታ መጠየቃቸውንም የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅም ከዚህ ህገ ወጥ ተግባር ጀርባ በመሆን በዋና ተዋናይነት ሲሳተፉ፣ ሲያስተባብሩ እና ሲያነሳሱ የነበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉ አካላትም ከከፍተኛ የጦር አመራር ደረጃ ጀምሮ እስከ ግልሰብ መሆኑንም ነው ጀነራል ሰዓረ መኮንን ያስታወቁት።

በቀጣይም ወታደራዊ ግምገማ በማድረግ በተግባሩ ላይ የተሳተፉ አካላት አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ገልፀዋል።

ጀነራል ሰዓረ መኮንን አክለውም፥ ከጥቅማጥቅም እና ከመልካም አስተዳደር እግሮች ጋር ተያይዘው ከሰራዊቱ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ሰራዊቱም ከዚህ በኋላ ጥያቄውን ህግን በተመለከተ መንገድ ማቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ጀነራል ሰዓረ መኮንን፥ ሰራዊቱ ከመንግስትና ከህዝቡ የተሰጠውን ግዳጅና ተልእኮ መሰረት እድርጎ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢወች ብሄርን፣ ጎሳን እና ሀይማኖትን መሰረት በማድረግ የሚነሱ ግጭቶችን የመከላከያ ሰራዊቱ ስነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና የማረጋጋት ስራ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ለአብነትም በሶማሌ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በጌዲኦ እና ጉጂ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የተከሰቱ ግጭቶችን ከህዝቡ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከወጣቶች ጋር በመሆን የመከላከል ስራ መስራቱንም ጠቅሰዋል።

የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን በመግለጫቸው አክለውም፥ መከላከያ ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት ራሱን በአዳዲስ አደረጃጀቶች እያዋቀረ መሆኑንም አንስተዋል።

መከላከያ ሰራዊቱ ሳንሳዊ የሆነ ብቃት እንዲኖረውም እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *