በሰሜን ጎንደር ዞን በቦንብ ፍንዳታ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ህይወት አለፈ
በሰሜን ጎንደር ዞን በቦንብ ፍንዳታ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ህይወት አለፈ
አርትስ 28/02/2011
በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት በህገ ወጥ መንገድ የተቀመጠ የእጅ ቦንብ ፈንድቶ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታዉቋል፡፡
የደባርቅ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል መረጃ ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ኢንስፔክተር ግርማይ አለባቸው እንደገለፁት ፤አደጋው የደረሰው ጥቅምት 24 ቀን 2011ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ በወረዳው አደባባይ ጽዩን ቀበሌበሚገኘው መኖሪያ ቤት ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ የተቀመጠ የእጅ ቦንቡን የቤቱ አባወራ በመነካካት ላይ እያሉ እጃቸው ላይ በመፈንዳቱ ነው፡፡
በፍንዳታውም አባወራውና ባለቤታቸው እንዲሁም የሁለት ልጆቻቸው ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሁለት የቤተሰብ አባላት የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ግለሰቦች በደባርቅ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቶ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ለከፍተኛ ህክምና መላካቸውን ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡
የአማራ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገበዉ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን በቤት ውስጥ ደብቆ ማስቀመጥ ወንጀል ከመሆኑም በላይ ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ድርጊት መቆጠብ እንዳለበትም ዋና ኢንስፔክተሩተናግረዋል፡፡