በሻሸመኔ ከተማ ተፈፅሟል የተባለው ድርጊት ከወር በፊት በእርቅ የተፈታ ጉዳይ ነው አለ የከተማ አስተዳደሩ
አርትስ 17/04/2011
በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ የተፈፀመ ድርጊት በሚል የተለቀቀው አሰቃቂ ቪዲዮ ብዙዎችን በማህበራዊ ሚዲያ እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ኢቢሲ ወደ ሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ደውሎ በማህበራዊ የትስስር ገፆች ላይ ስለተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ለማጣራት እንደሞከረው፣ ድርጊቱ የተፈፀመው በከተማዋ ይሁን እንጂ ከአንድ ወር ከ11 ቀን በፊት የተፈፀመ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ኮሙዪኒኬሽን ኃላፊው አቶ ሀሮን ከድር ለኢቢሲ እንደገለፁት ጉዳዩ ህዳር 6፣2011 የተፈፀመ ፀብ ነበር፡፡
ፀቡን ተከትሎም ጉዳት በደረሰባቸው እና ድርጊቱን በፈፀሙት ወገኖች መካከል የፀጥታ አካላት፣የከተማው ከንቲባና የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት እርቀ ሰላም ከተፈፀመ ውሎ ማደሩንና ጉዳዩ አሁን ላይ በቪዲዮ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መለቀቁ የከተማዋን ገፅታ ሆን ብሎ ለማጠልሸት የታለመ መሆኑን አቶ ሀሮን ተናግረዋል፡፡
በሻሸመኔ ከተማ አሁን ላይ ምንም አይነት የተፈጠረ ችግር የለም ፤ከተማዋም የተረጋጋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተከናወነባት መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡