ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴይንሜዬር ጋር ተወያዩ
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴይንሜዬር ጋር ተወያዩ
ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴይንሜዬር በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በዛሬው ዕለት ጀምረዋል።
በቆይታቸውም ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ እና ተያየዥ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ነው የተገለፀው።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ትክክለኛ ሰዓት መሆኑን በመጠቆም፥ ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለውጥ እያካሄደች መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር የምትፈልግ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ በትብብር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላት መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ዋልተር በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ያደነቁ ሲሆን ፥ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖውም በጋራና በትብብር ለመስራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም አዲሱ የኢትዮጵያ አስተዳደር ሴቶችን ወደ ስልጣን በማምጣት ሴቶች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ የተሰራውን ስራ አድንቀዋል።
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበራትን ልዩነት በመፍታት በቀጠናው የነበረውን የሰላም ችግር ለመፍታት የተወሰደውን እርምጃ አድንቀዋል ።
ስለሆነም ጀርመን በንግድ፣በኢንቨስትመንት፣በስልጠናና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብርና በቅርበት የምትሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንት ዋልተር ተናግረዋል።
በሀገራቸው የሚገኙ ትልልቅ ኩባንያዎች ያላቸውን እምቅ ዕውቀትና ገንዘብ ተጠቅመው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ፍላጎት ያላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል
ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴይንሜዬር በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ምንጭ ፡-ፋና