4ኛው የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ በመጭው ዕሁድ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ማህበሩ አስታወቀ፡፡
4ኛው የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ በመጭው ዕሁድ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ማህበሩ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ የህክምና ማህበር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የሚያሰናዳው ይህ 4ኛ ዓመት የማሕበሩ የሩጫ ውድድር፤ ዋንኛ ዓላማው የህብረተሰቡን ጤና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ሩጫው እንደተጋጀ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገመችስ ማሞ ጉዳዩን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ገመችስ ጨምረው በውድድሩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከጤንነት በተጨማሪ ለደህንነታችን የሚግዙን በመሆኑ አስፈላጊነቱን ለማጉላትና ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ለደህንነታችን እንሩጥ›› የሚል መሪ ሀሳብ ያነገበው ይህ የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ 50 ሴት፣ 50 ወንድ አትሌቶች፤ የህክምና ባለሙያዎች እና ሌሎች የህብረተስብ ክፍሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 2600 ገደማ ሰዎች እንደሚካፈሉበት የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኃላፊ አቶ ዱቤ ጅሎ በኩል ተገልጧል፡፡
አቶ ዱቤ በሁለቱም ፆታ ለሚካፈሉ ከ1 – 3 ደረጃን በመያዝ ለሚያጠናቅቁ አሸናፊ አትሌቶች የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ሲዘጋጅ ከ4-6 ደግሞ የብር ሽልማት ሲዘጋጅ፤ ከተሳታፊዎች በኩል ከ1 -3 ደረጃ በመያዝ ለሚጨርሱ ደግሞ የሜዳሊያ ሽልማት ይበረክትላቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በውድድሩ አንደኛ ለሚወጣው አትሌት 15 ሺ ብር፣ ለሁለተኛው 10 ሺ እና ሶስተኛ በመሆን ለሚያጠናቅቀው አትሌት ደግሞ 7 ሺ ብር የሚሸለም ሲሆን በአጠቃላይ ለውድድሩ 76 ሺ ብር ተዘጋጅቷል፡፡
የዘንድሮው ውድድር መነሻውን ዲያስፖራ አደባባይ በማድረግ መዳረሻውን መገናኛ ማራቶን ህንፃ የሚጠናቀቅ መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ የህክምና ማህበር ህብረተሰቡ ጤናውን እየጠበቀ በሩጫው ላይ አንዲሳተፍ ጥሪውን አቅርቧል፡፡