በርካታ የኢሮፓ ሊግ ተጠባቂ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይከናወናሉ፡፡
በርካታ የኢሮፓ ሊግ ተጠባቂ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይከናወናሉ፡፡
በ32 ቡድኖች መካከል የሚካሄደው የማጣሪያ የመልስ ጨዋታዎች በምሽቱ በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ይከናወናሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት ወደ ቤላሩስ ተጉዞ የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዶ የተመለሰው አርሰናል ኤመሬትስ ላይ ባቴ ቦሪሶቭን ምሽት 2፡55 ያስተናግዳል፡፡ በምሽቱ ግጥሚያ በመድፈኞቹ በኩል በመጀመሪያው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው አሌክሳንደር ላካዜት የማይኖር ሲሆን፤ ፔር ኤምሪክ ኦባማያንግ ከጥቅምት ወር በኋላ በኢሮፓ ሊግ ይሰለፋል፡፡
ሜይትላንድ ኒልስ በህመም ምክንያት የዕረቡ ልምምድ ያመለጠው ሲሆን አማካዩ አሮን ራምሴ እና ተከላካዩ ሶቅራትስ ፓፓስታቶፖሎስ ግን ከጉዳት ተመልሰዋል፡፡
አሰልጣኝ ኡናይ ኢመሪ ለሜሱት ኦዚል የመለሰለፍ ዕድል ሊሰጡት እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት ሌሎች ግጥሚያዎች የሚደረጉ ሲሆን ናፖሊ ከ ዙሪክ፣ ቫሌንሲያ ከ ሴልቲክ፣ ቪያሪያል ከ ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ አይንትራክት ፍራንክፉርት ከ ሻክታር ዶኔስክ፣ ዜኒት ፒተርስበርግ ከ ፌነርባቼ፣ ዲናሞ ዛግሪብ ከ ቪክቶሪያ ፕለዘን፣ አር.ቢ ሳልዝበርግ ከ ክለብ ብሩዥ ይጫወታሉ፡፡
ምሽት 5፡00 ላይ ደግሞ በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው የእንግሊዙ ቼልሲ ስታንፎርድ ብሪጅ ላይ የስውዲኑን ማልሞ ያስተናግዳል፡፡ ባለፈው ሳምንት ሁለቱ ቡድኖች ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ሰማያዊዎቹ 2 ለ 1 ረትተዋል፡፡
ግብ ጠባቂው ኬፓ አሪዛባላጋ በቋንጃ ጉዳት ምክንያት ለቡድኑ ግልጋሎት የማይሰጥ ሲሆን በዊሊ ካባዬሮ የሚተካ ይሆናል፤ አጥቂው ፔድሮ በሆድ ህመም እና ተከላካዩ ዳቪደ ዛፓኮስታ ትኩሳት ስላለባቸው የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡
ስራቸው ችግር ውስጥ የሚገኘው አሰልጣኝ ማውሪዚዮ ሳሪ የምሽቱ ግጥሚያ ውጤት የእርሳቸውን ቆይታ ይወስን እንደሆነ ተጠይቀው፤ ሶስት እና አራት ጨዋታዎችን በተከታታይ ማሸነፍ ብቸኛው መፍትሄ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ምሽት 5፡00 ላይ በሚከናወኑ ሌሎች ጨዋታዎች ባየር ሊቨርኩሰን ከ ክራስኖዳር፣ ቤንፊካ ከ ጋላታሳራይ፣ ዳይናሞ ኬቭ ከ ኦሊምፒያኮስ፣ ኢንተር ሚላን ከ ራፒድ ቬና፣ ሄንክ ከ ስላቪያ ፕራህ፣ ሪያል ቤቲስ ከ ሬን ይገናኛሉ፡፡
ትናንት ምሽት ሲቪያ በራሞን ሳንቼዝ ፒዡዋን ስታዲየም ላትሲዮን 2 ለ 0 በአጠቃላይ 3 ለ 0 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡