loading
“ወቅቱ በከተማችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የስራ አጥ ወጣት ይዘን የምናንቀላፋበት አይደለም አሉ ከንቲባ ታከለ ኡማ፡፡

ወቅቱ በከተማችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የስራ አጥ ወጣት ይዘን የምናንቀላፋበት አይደለም አሉ ከንቲባ ታከለ ኡማ፡፡

ከንቲባዉ  በሚቀጥሉት ወራት ያለምንም ፋታ ትኩረት ሰጥተን የምንመራው ዘርፍ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ይሆናልም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ለወጣቶች በመደበው የ2 ቢሊዮን ተዘዋዋሪ ፈንድ ዙርያ ምክክር ተደርጓል፡፡ ይህንን ፈንድ ወደ ስራ ለማስገባትና ወጣቶችን ለመመልመል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይነት እተገብራቸዋለሁ ያለዉን  የስራ ዘርፎች ይፋ አድርጓል፡፡
በ100 ወረዳዎች የነዳጅ ማደያዎች ገንብቶ ለተደራጁ ወጣቶች ማስተላለፍ፤በ116 ወረዳዎች የከተማዋን ደረጃ እና ውበት በጠበቀ መልኩ በአዲስ ዲዛይን የተሰሩ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆችን ገንብቶ ማስተላለፍ ፤ከ2000 በላይ ዘመናዊ የንግድ ሱቆች ግንባታ፤ ያገለገሉ 300 የከተማ አውቶቢሶችን በመጠቀም ተንቀሳቃሽ የምግብ እና መጠጥ መሸጫ(Van food truck) ለወጣቶች መስጠት እና በከተማዋና በዙርያዋ ባሉ የኢንዳስትሪ ፓርኮች ውስጥ ወጣቶችን በማኑፋክቸርንግ ዘርፍ ማሠማራት ከእቅዶቹ መካከል ይገኙበታል፡፡
የዳቦ መጋገሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት በርካታ ወጣቶችን በዘርፉ ማሰማራት አስተዳደሩ ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል ናቸው፡፡

በመድረኩ የስራ መመሪያ ያስተላለፉት ኢ/ር ታከለ ኡማ ከተጠቀሱት የስራ አማራጮች በተጨማሪ ወጣቶች የራሳቸውን የስራ ሃሳብ በማምጣት መሳተፍ የሚችሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ከቦታ ልየታ ጀምሮ የዲዛይን እና የግንባታ ስራዎችን ጭምር ወጣቶቹ በባለቤትነት እየተቆጣጠሩ ከአስተዳደሩ ጋር በጋራ መስራት አለባቸውም ብለዋል፡፡

የብድር አሰጣጡና የወጣቶች ምልመላው ከምንም በላይ በጥንቃቄ እና በፍትሃዊነት መሠራት አለበት ያሉት ኢ/ር ታከለ ኡማ የተንዛዙ አሰራሮች ላይ ማሻሻያ በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት መሠጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ይህንን ስራ ትኩረት በመስጠት በየሳምንቱ በከተማው ከፍተኛ አመራሮች ግምገማ እየተደረገበት በልዩ ትኩረት እንደሚተገበር ሰምተናል፡፡

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *